የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገለጹ

53

ሚያዝያ 24/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብት በማድረግ ላይ ካሉት የእንግሊዙ አቻቸው ጀርሚ ሃንት ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የሚኒስትሮቹ ውይይት ትኩረቱን ያደረገው በሁለትዮሽ አገራዊ የትብብር ጉዳዮች ዙሪያ መሆኑንም ከኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥና በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ መሆኗን የጠቀሱት አቶ ገዱ በዚህ ረገድ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው አገራት ሰላም እንዲሰፍን እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ገልጸው ከኤርትራ ጋር ስለተደረስው የሰላም ስምምነትም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኗንም እንዲሁ።

ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲመሰረት ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰራች ትገኛለችም ብለዋል።

እንግሊዝ በኢትዮጵያ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ጉልህ ድርሻ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

የእንግሊዙ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየወሰደች ያለውን የሪፎርም ሂደት አድንቀው ለዚህም አገራቸው ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማትን አቅም በማሳደግ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለችም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም እንዲስፍን እያደረገች ያለውን ሰፊ ስራ አድንቀው እንግሊዝ በዚህ ዙሪያም በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥልም እንዲሁ።

ኢትዮጵያና እንግሊዝ በኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲና ባህል ዘርፎች የቆየና ጥብቅ የሆነ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንግሊዝ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ከከፈቱ የዓለም አገሮች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ስትሆን ኢትዮጵያም በለንዴን ኤምባሲዋን በመክፈት ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተርታ ትጠቀሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም