መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ ተጠየቀ

88

ሚያዝያ 24/2011የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ የተካሄደው ሰልፍ አስተባባሪዎች ጠየቁ፡፡

የዜጎች ሞትና መፈናቀል ይቁም በሚል ዛሬ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሄደው  ስላማዊ ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል፡፡

የባህርዳር ሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ ወጣት እንዳላማው ክንዴ እንደገለጸው የዛሬው ሰልፍ ዓላማ በአማራ  ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግድያና መፈናቀል የፌዴራልና የክልሉ መንግስት በዝምታ መመልከታቸውን በመቃወም ነው።

በዋናነት በአጣየ፣ ከሚሴ፣ ቀደም ሲል በጎንደር አሁን ደግሞ በመተከል በንጹሃን  ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም መንግስት ዝምታ መምረጡ እንዳሳዘነው ተናግሯል።

"ሰልፉ እንደከዚህ ቀደሙ ፈቃድ ጠይቀንና አግኝተን ሳይሆን ያደረግነው በሰላም ተቃውሟችንን በአደባባይ በማሰማት ለመመለስ ያደረግነው ስለነበር ተሳክቷል "ብሏል።

የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ህዝቦች በፈለጉት አካባቢ ሰርተው የመኖር መብታቸው እንዲጠበቅ ለመጠየቅ ሰልፍ መውጣታቸውን የተናገረው ደግሞ ሌላኛው የሰልፉ አስተባባሪ ወጣት እንዳልካቸው ጥላሁን ነው።

"አማራነት ዘረኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ነው" ያለው ወጣት እንዳልካቸው የፌዴራል መንግስትም መምራት ካለበት የሀገሪቱን ህዝቦች ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ እንዲሆን ጠይቋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚደንት ወጣት ትህትና በላይ በበኩሏ "በየቦታው እየተጨፈጨፉ ለሚገኙ ወገኖቻችን የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ፍትህ ሊሰጣቸው ይገባል" ብላለች።

ለመንግስት የሚያሳውቁትም የመጨረሻው የተቃውሞ ሰልፋቸው እንደሆነ አመልክታለች።

መንግስት መልዕክታቸውን  ሰምቶ ዜጎቹ  በየትኛውም ቦታ በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ደህንነታቸውን እንዲያስጠብቅ ጠይቃለች።

በተመሳሳይ ሰልፉ በጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ መራዊ፣ ደጀንና ደብረታቦር ከተሞች ሲካሄድ ተሳታፊዎቹ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በክልሉ ከተሞች የተካሄደው ይሄው  ስላማዊ  ሰልፍ   በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም