የሐረሪና የኦሮሚያ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፍረንስ ተካሄደ

90

ሐረር ሚዝያ  24 /2011 የሐረሪና የኦሮሚያ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ በሐረር ከተማ ተካሂደ።

 በኮንፍረንሱ የሁለቱ  ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የነዋሪ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደተናገሩት በሐረሪ ክልል የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት ማጎልበት ይገባቸዋል።

ሐረር የምትታወቅበትን የፍቅር፣የሰላም፣የመቻቻልና አብሮ መኖር አኩሪ ባህል ነዋሪው እንዲያጎለበትም እንዲሁ።

በክልሎች መካከል መቃቃርንና መከፋፈልን ለመፍጠር የሚሯሯጡ ኃይሎችን መታገልና ህዝቦች አንድነታቸውን በማጠናከር የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባም  አቶ ሽመልስ አመልክተዋል።

የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስና ሐሳብን የመግለጽ፣ ሰርቶ የመኖርና ሐብት የማፍራት መብቶች በማስከበርና አንድነትን በማጎልበት  ረገድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀል።

የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ሐረር  የተለያዩ እምነትና ባህል ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት መሆኗ ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቷን ጠቅሰዋል።

ይህን አኩሪ ባህል ማሳደግ የሚገባው ሁሉም የክልሉ ነዋሪ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ የተገኘውን ለውጥ ለማደናቀፍ የተሰለፉ አንድ አንድ የጥፋት ኃይሎች በክልሉ ነዋሪዎች መካከል ልዩነትን ለመፍጠር ያሴሩት እኩይ ተግባር በህዝቡ ተሳትፎ ከሽፏል" ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ የሰላም ኮንፍረንሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው  መሰል መድረኮችን የማዘጋጀቱ ስራ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህዝብን ድምጽ መስማት፣ ፍትሃዊ አሰራሮችንና ተጠቃሚነትን ማስፈን፣ ወገንተኝነትን መታገል እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የምሰራቅ ሐረርጌ አፈረን ቀሎ ሁምበና አባ ገዳ ሙሳ ሮባ በሰጡት አስተያየት የመድረኩ መዘጋጀት ህዝቡን ይበልጥ በማቀራረብ አንድነቱን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳለው  ተናግረዋል።

አመራሩም የጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንዲያጠናክርና ህዝብን ያሳተፈ  ስራዎችን እንዲያከናውን መድረኩ አቅም እንደሚፈጥረለትም ጠቁመዋል።

"የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣አባ ገዳዎችና ወጣቶች ሰላምን ለማስፈን የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እድል ይሰጣል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም