ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዩኔስኮ የ2019 የሰላም ተሸላሚ ሆኑ

174

ሚያዝያ 24/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ የ2019 የሰላም ተሸላሚ ሆኑ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሽልማት ያገኙት በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት፣ ለማስጠበቅና ለማቆየት እንዲሁም የፕረስ ነፃነት እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋፅኦ መሆኑ ተገልጿል።

ከትናንትና ጀምሮ በልዩ ልዩ ሁነቶች በአዲስ አበባ እየተከበረ ባለው የዓለም የፕረስ ነፃነት ቀን ላይ የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር አድሪ አዙላይ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት በነበረው መድረክ ላይ ተገኝተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዘንድሮውን የድርጅቱ የሰላም ተሸላሚ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና የፈረንሳይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎንዴ የተካተቱበት የዩኔስኮ የተሸላሚዎች መራጭ ኮሚቴ ነው ምርጫውን ያከናወነው።

የዩኔስኮ ፌሊኒክስ ሃፌፍ- ቦኒይ የሰላም ሽልማት ለሃያ በላይ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ግለሰቦች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ የተሰጠ ሲሆን ሽልማቱን አስመልክቶ ፕሬዝዳንት ሰዓለወርቅ ዘውዴ እንኳን ደስ አለን ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ሽልማቱ “ዓለም አቀፍ ግጭቶችን በመፍታት፣ የውይይትንና ድርድርን ሚና በማጉላትና በመቻቻል፣ በእኩልነትና በመግባባት ሰላም እንዲሰፍን አስተዋፅኦ ለሚያደርጉ ግለሰቦች” የሚሰጥ መሆኑን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም