መንግስት ወደ ቄያችን እንዲመልሰን እንጠይቃለን-- ተፈናቃዮች

55

ሚያዝያ 24/2011 መንግስት የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ወደ ቄያቸው እንዲመልሳቸው በሰሜን ወሎ ዞን የተጠለሉ ተፈናቃዮች ጠየቁ።

በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት በሚኖሩበት አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በመፍታት እንዲመልሳቸው ይፈልጋሉ።

አቶ መንግስቱ ከበደ  ነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ከነበሩበት ተፈናቅለው  አምስት ቤተሰባቸውን ይዘው በቆቦ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት የምግብ ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ መልካም ቢሆንም ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለወራት በጊዜያዊ መጠለያ መቆየታቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አመልክተዋል፡፡

"ሰርተን መብላት እየቻልን፣ ሰርተን ሃብትና ንብረት የማፍራት አቅሙ እያለን መንግስት ፈጥኖ መድረስ ባለመቻሉ በሰው ሰራሽ ችግር ሳንፈልግ ለተረጅነት ተጋልጠናል" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከእርዳታ ይልቅ ሰርቶ መኖር እንደሚፈልጉ የገለጹት ተፈናቃዩ መንግስት በአስቸኳይ የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

መንግስት በቦታው የጸጥታ አካላትን በማሰማራትም  ይኖሩ ወደ ነበረበት አካባቢ መልሷቸው የተረጋጋ ኑሮ ለመጀመር ይፈልገሉ።

ከአላማጣ ተፈናቅለው በዚሁ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙት አቶ ሞገስ ትኩየ  በበኩላቸው ከሚኖሩበት አካባቢ መፈናቀላቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። 

"ከ10 ወራት በላይ ያለስራ ተቀምጠን ተረድተናል" ያሉት አቶ ሞገስ የክረምት የእርሻ ወቅት ሳያልፍ መንግስት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

ወይዘሮ አሰፉ ካሳየ  በበኩላቸው በቂ ባይሆንም በየወሩ በሚሰጣቸው ስንዴና ዘይት የእሳቸውንና የአምስት ልጆቻቸውን ሕይወት ለማቆየት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ለአንድ ዓመት ተኩል በራያ ቆቦ አቧሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጊዜያዊ መጠለያ እየኖሩ መሆናቸውን ጠቅሰው  በቅርቡ ያረፉበት ድንኳን በነፋስ በመፍረሱ ወደ አካባቢው ነዋሪዎች ቤት ለመጠጋት መገደዳቸውን አመልክተዋል፡፡

በጊዜያዊ እርዳታ አስከፊ ጊዜ እያሳለፉ መሆናቸውንና   መንግስት አስቼኳይ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋ ውቤ እንደገለጹት በዞኑ በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ አራት ሺህ ተፈናቃዮች በየወሩ በቋሚነት እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

ከኦሮሚያ፣ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከደቡብ፣ ከአፋርና ከሶማሌ ክልሎች የመጡ ተፈናቃዮቹ   በአራት መጠለያዎችና ከቤተሰብ ጋር ተጠግተው እየኖሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ላለፉት ሰባት ወራት 500 ኩንታል የምግብ እህል፣ አንድ ሺህ 327 ሊትር ዘይትና ለተጎዱ ህፃናት ደግሞ አልሚ ምግብ በየወሩ  ሳይቆራረጥ መከፋፈሉን አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት አካባቢ በመመለስ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ከተያዘው  ወር መግቢያ ጀምሮ የማወያየትና የማሳመን ስራ እየተካሄደ  ነው።

በውይይቱ ከፊል ተፈናቃዮች መንግስት ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመልሳቸው መስማማታቸውን ያስታወቁት ኃላፊው አንዳንድ ተፈናቃዮች ከጸጥታ ችግር ስጋት አንጻር ወደ ነበሩበት አካባቢ ለመመለስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።

"ዜጎች ከተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች ካሉ አመራሮች ጋር የተጀመረውን ምክክር በማጠናከርና የአካባቢዎችን ሰላም በማረጋገጥ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው "ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ሲመለሱም መንግስት መጓጓዣን ጨምሮ አምርተው ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ አስፈላጊውን ወጪ እንደሚሸፍን  ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም