ለኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መጠናከር የትግራይ ክልል ህዝብና መንግስት በትኩረት ይሰራል--ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

134

መቀሌ ሚያዚያ 24/2011የኢትዮ ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የትግራይ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በክልላዊና ሃገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳለመከቱት በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ህወሓት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለኢህአዴግ ሲያቀርበው የነበረ አጀንዳ ነበር።

ኢህአዴግም ጉዳዩን በትኩረት በማየት የሁለቱም ሀገራት መሪዎች በጀመሩት ግንኙነት ወደ ህዝብ ይበልጥ መውረድ እንዳለበት የክልሉ መንግስት እምነት መሆኑን ተናግረው “የሰላም ሂደቱ የፌዴራል መንግስት እንጂ የትግራይ መንግስት አልተቀበለውም እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ መሰረት የሌለው ነው” ብለዋል።

“ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ከፌዴራል መንግስቱ የተለየ አቋም የለንም” ያሉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ አሁንም የክልሉ ህዝብና መንግስት ከኤርትራ ህዝብ ጋር አብሮ ለማደግ የላቀ ፍላጎት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የፌዴራል ስርዓቱና ህገመንግስቱ አሁንም አደጋ ላይ መሆኑን ገልጸው ማንነትን መሰረት አድርገው የተደራጁ ፓርቲዎችን ለማጥፋት የሚደረገው ሽርጉድ ችግር እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

በየአካባቢው ለሚከሰቱ ግጭቶችና የሰዎች ህይወት መጥፋት የአመራሩ ችግር መሆኑን አውቆ ወደ መፍትሄ ከመሄድ ይልቅ ውጫዊ የማድረግ ሁኔታ አሁንም ያልተፈታ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፉት አመታት ክልሉ በተለየ ሁኔታ ተጠቅሟል በሚል የተሳሳተ አመለካከት በፌዴራል መንግስት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች መጓተትና አዳዲስ እንዳይሰሩ የማድረግ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው ችግሩ ከተሳሳተ ግንዛቤ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የህዝቡን አንድነትና ጥንካሬ ለመፈታተን ይደረጉ የነበሩ ትንኮሳዎች ቀዝቅዘው በምትኩ አንድነቱን ለማጠናከር ሌሎች አጀንዳዎች እየተቀረፁ መሆናቸውን ገልፀው ህገ-መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱ እየደረሰበት ካለው አደጋ ለመታደግ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ዶክተር ደብረጽዮን አስረድተዋል።

መንግስት የክልሉ ሰላም ይበልጥ እንዲጠናከር ከመስራት አልፎ ለመልካም አስተዳደር ችግሮችና ለልማት ስራዎች እንቅፋት የሆኑትን በመፍታት የተለየ ትኩረት እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላም ኢንቨስትመንቱን ከማጠናከር ጀምሮ ለሌሎች ክልሎችና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ምሳሌ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቀበሌ መዋቅሩን የማጠናከርና አደረጃጀቱን የማስተካከል፣የግብርና ስራውን የማጠናከር፣የቁጠባ ባህልን በማዳበር ከተለያዩ ክልሎች ለተፈናቀሉት የመስሪያ ቦታና የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መምጣቱን ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በትላንት ማምሻ መግለጫቸው ላይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በህይወት ዘመናቸው ከህገ-መንግስት ረቂቅ ጀምሮ የፌዴራል ስርዓቱን እስከ ማጠናከር ድረስ የነበራቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ በማድነቅ በሞት በመለየታቸው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ የስፖርት ውድድር አድርገው ወደ ክልላቸው በመምጣት ላይ እያሉ በደረሰባቸው አደጋ ለጠፋው ህይወት እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ ሁከት ለሞቱት ወገኖች ማዘናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም