የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦችን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ ነን -የሁለቱ ክልል መሪዎች

80

አዲስ አበባ ሚያዝያ23/2011 ለበርካታ ዘመናት ችግርና ደስታን በጋራ ያሳለፉ የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦችን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን የሁለቱ ክልል መሪዎች ተናገሩ።

የኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች የሰላምና ወንድማማችነት ጉባኤ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በጉባኤው ከሁለቱ ክልሎች የተወከሉ የኃይማኖት አባቶች፣የጎሳ መሪዎች፣  የአገር ሽማግሌዎችና ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት ነጻነትና እኩልነት የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ በሚፈለገው ደረጃ አንዲሰፍን ዋና ማሳሪያው ወንድማማችነት ነው ብለዋል።

ይህ እውን እንዲሆን የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች በጋራ መስዋትነት እንደከፈሉ በማከል።

ትናንት ሁለቱን ህዝቦች ለመለያያት ሲሸረብ የነበረውን ሴራ በጣጥሰው አንድነታቸውን ለመገንባት የትናንትናውን ስህተት በይቅርታ መሻራቸውን አብስረዋል።

"የህዝቦች አንድነት ከሴራ በላይ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የትኛውም ሴራ የህዝቦችን አንድነት ሊለያይ እንደማይችል ተናግረዋል።

የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት መጠናከር ለኢትዮጵያ አንድነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመጠቆም።

"ኦሮሞነት ማቀፍ፣ ነው ሁሉን እንደ አንድ ማየት ነው፣ ከራስ በላይ ለሌላው መስጠት ነው፣ በመሆኑም ይህን መልካም ባህል አጎልብተን አንድነቷ የተጠናከረ አገር እንገነባለን'' ሲሉም ተደምጠዋል።

"ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚመኙ ሃይሎች እየተካሄደ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ለማምከን ከብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራና በማቀፍ መንፈስ እንሰራለን" ብለዋ።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው ''የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህልና አንድ ደም ያለን ህዝቦች በመሆናችን መቼም ቢሆን ልንለያይ አንችልም" ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ለኦሮሞ ፤ የኦሮሚያ ክልል ለሶማሌ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበት ቦታ መሆኑንም አብራርተዋል።

''የህዝቦቹ አንድነት ለኢትዮጵያና ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር ኃይል ነው'' ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከአሁን በኋላ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት የሚያናጋ ምንም ኃይል እንደማይኖር ተናግረዋል።

''ሁለቱ ህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን አጠናክረው አብረው ሰርተው መልማት አለባቸው'' ሲሉም አክለዋል።

ኦሮሞና ሶማሌ እንደተጋጩ ተደርጎ የሚነገረው አገላላጽ አግባብ አይደለም ያሉት አቶ ሙስጠፋ፤ "ግጭቱ ህዝባዊ መሰረት ያለው ሳይሆን በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ በምስራቁ በኩል በጥቂቶች የተቀነባበረ ሴራ ውጤት ነው" ብለዋል።

ወደፊት ይህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይደገምና ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወንድም የኦሮሞ ህዝቦች ወደቀያቸው እንዲመለሱ አስተዳዳራቸው አስፈላጊውን እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም