የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና ሰጠ

98
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለሁለት አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና ሲሰጥ የአንድ ሌላ ፓርቲ ፈቃድ ደግሞ ሰርዟል። ለሁለቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና የተሰጠው በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም መሰረት መሆኑን የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ ለኢዜአ ተናግረዋል። ቦርዱ እውቅና ከሰጣቸው መካከል አንዱ አገር አቀፍ ፓርቲ ሲሆን አንደኛው ደግሞ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። በቀረበው ጥያቄ መሰረት እውቅና የተሰጣቸው ፓርቲዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ  የተባለ ሀገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ  የተባለ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ናቸው። ዕውቅና ለጠየቁ እነዚህ ፓርቲዎችም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ /አህነፓ/ ከምዝገባ እንዲሰረዝ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ቦርዱ ስረዛ ማድረጉን አሳውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም