ዶክተር ነጋሶ ለህዝብ መብት በመታገል የአገር ጥቅም ያስቀደሙ ታማኝ ሰው ነበሩ - ምሁራን ና ፓርቲዎች

79

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2011 የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ "ለህዝብ መብት በመታገል የአገር ጥቅም ያስቀደሙ ታማኝ ሰው ነበሩ" ሲሉ የፖለቲካ ምሁርና ፓርቲዎች ገለጹ።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጀርመን በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የሚታወስ ነው።

ኢዜአ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ የፖለቲካ ምሁርና ፓርቲዎችን አነጋግሯል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደንብ እንሚያውቋቸው ይናገራሉ።

ዶክተር ነጋሶ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ በነበሩበት ወቅትና ከፓርቲ ፖለቲካ ከወጡ በኋላም የኢትዮጵያን ህዝብ ባላቸው አቅም ሲያገለግሉ ነበር ብለዋል።

የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ህዝብን አገለግላለሁ ለህዝብ ብሶት እታገላለሁ በማለት 1997 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በግል እጩ ሆነው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው በማሸነፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንደሆኑም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅትም "የኢህአዴግን አገዛዝ በግልጽ በመቃወም የነበረውን ስርአት እንደማይቀበሉ በመግለጽ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውና ይህም በኢትዮጵያ ህዝብ ይበልጥ እንዲታወቁ ያደረገ" ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ከፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው ከለቀቁ በኋላ በግላቸው ለኢትዮጵያ ለያዙት አላማም በጽናት ሲታገሉ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ህገ መንግስቱ እንዲጸድቅ በፊርማቸው ያረጋገጡት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከሶስት ዓመት በፊት "ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ" የተባለ የአሜሪካ ተቋም ባደረገው ጥናት ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸውና ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል ጥረት ሲያደርጉ ነበርም ብለዋል።

"በነበራቸው የፖለቲካ ቆይታ ለፖለቲካ ትርፍ እና ጥቅም ሳይሆን በታማኝነት ህዝብን ለመጥቀም በተቻላቸው አቅም ሲለፉና ሲታገሉ የቆዩና ለህዝብ መብት ከታገሉ ቁልፍ ሰዎች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው" ብለዋል።

ዶክተር ነጋሶ ከግል ጥቅም ይልቅ የአገር ጥቅምን ያስቀደሙና ስልጣን ማለት ህዝብን አገልጋይነት መሆኑን ያስተማሩ ሰው እንደሆኑም ነው ፕሮፌሰር መረራ የተናገሩት።

በተለይ የነገይቱን ኢትዮጵያ መምራት ለሚፈልጉ በሐቅ ለህዝብ መብት መታገል መሞከርን ከዶክተር ነጋሶ መማር ይቻላል ብለዋል።

ፖለቲከኞች ፖለቲካ ውስጥ ለጥቅም ሳይሆን ህዝብን ለማገልገልና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ መግባት እንዳለባቸው የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የፖለቲካ ቆይታ ምሳሌ ሊሆን የሚችል እንደሆነም አመልክተዋል።

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉ ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ 2004 እስከ 2006 ዓ.ም አብረው እንደሰሩ ይገልጻሉ።

ዶክተር ነጋሶ በፓርቲው ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ስራቸውን በቁርጠኝነት እና በትጋት ሲሰሩ  እንደነበሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዶክተር ነጋሶ በዴሞክራሲ እና በህግ የበላይነት የሚያምኑ፣ በነበሩት ፓርቲ ህግና ደንብ ተገዢ ሆነው ፓርቲውን በተቀመጠላቸው ህግና ስርዓት ማስተዳደራቸውን አመልክተዋል።

በፓርቲ ውስጥ እሳቸው የማይደግፉት ሀሳብ በፓርቲው ምክር ቤት ሲጸድቅ ከማንም በላይ ሀሳቡ እንዲተገበር በጽናት ሲሰሩ እንደነበርም አመልክተዋል።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ ከተማሪዎች ንቅናቄ አንስቶ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ ሲደረግ በነበረው ጥረት ውስጥ ያላሰለሰ ጥረት እንዳደረጉም ተናግረዋል።

ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በነበራቸው ልምድ በፖለቲካ ውስጥ የሚደርስባቸውን ተጽእኖና ጫና በጥላቻ ፖለቲካ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በመታገል የሚያሸንፉ ብልህ ሰው እንደነበሩም ነው አቶ ትዕግስቱ ያስረዱት።

ከፖለቲካ ህይወታቸው ውጪ ያላቸው በማንነታቸው መልካም የሚባል ስብዕና ያላቸው ሰው እንደነበሩም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው ዶክተር ነጋሶ በአፄ ኃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ የተለያየ ጫና እየደረሰባቸው ለአላማቸው በጽናት መታገላቸውን ገልጸዋል።

ለያዙት አላማ በጽናት መታገል የእድሜ ልክ የረጅም ጊዜ ትግል እንደሚጠይቅ ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ መማር እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከሚገጥሟቸው ፈተናዎችና ችግሮች ይልቅ የኢትዮጵያን የወደፊት መልካም ነገር በማየት ለአገራቸው ብልጽግናና እድገት ሲሰሩ የነበሩ ብሩህ አመለካከት ያላቸው ሰው ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ውስጥ ሁሉም ጥያቄዎች መመለስ እንደሚችሉና ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደሙ ለአገራቸው የለፉ ታማሽ የህዝብ አገልልጋይ ናቸው ብለዋል።

"ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ትሁት፣ ቅን፣ ግልጽ እንዲሁም በዛው ልክ ጠንካራና የማይበገሩ ሰው ነበሩ፤ ይህንንም ስብዕናቸውን ትውልዱ በመላበስ ለኢትዮጵያ እደግትና ብዕጽግና መስራት ይጠበቅበታል" ነው ያሉት።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ብሔራዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ለማካሄድ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን አስተባባሪ ኮሚቴው በሚያወጣው የስርዓተ ቀብር መርሃ ግብር አማካኝነት ቀብራቸው ይፈጸማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም