የጌዴኦና ጉጂ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው -የሰላም ሚኒስቴር

87

ሀዋሳ ኢዜአ ሚያዝያ 23 /2011 የጌዴኦና ጉጂ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስና ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት ለማስቆም እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የፌዴራል፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች አመራሮች የተሳተፉበት ተፈናቃዮችን በማቋቋም ዙሪያ የሚመክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በወቅቱ እንደገለፁት ተፈናቃዮች በቂ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙና መልሰው እንዲቋቋሙ ለማስቻል በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ።

የሚቋቋሙ ዜጎችም ተመልሰው እንዳይፈናቀሉና ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት ለማስቆም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል ።

"ከዞኖቹ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የማስመለሱ ስራ አለም አቀፍ መስፈርቶችን ባሟላና ሰብዓዊ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝና  የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በፌደራል መርማሪ ቡድኖችና በሁለቱ ክልሎች ትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንዳሉት ተፈናቃዮችን የማቋቋምና ድርጊቱ ዳግም እንዳይከሰት የማስቆም ስራ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሰላም ሚኒስቴርና በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የቅርብ ክትትል እየተደረገ ነው።

በቀጣይ ቀናት ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ዜጎች በቂ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መቅረቡን ጠቅሰው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ድጋፉ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።

"ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ተፈናቃቶች የሚደረገው ድጋፍ ፍትሀዊነቱን ጠብቆ ሳይቋረጥ እንዲደርስ ለማስቻል በቡሌ ሆራና ቀርጫ ወረዳዎች የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከልና ኮማንድ ፖስት ይቋቋማል" ብለዋል።

ከጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ 15 ሺህ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ በተያዘው  ሳምንት ውስጥ እንደሚከናወን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አህመድ ቱሳ ናቸው።

በቀርጫ ወረዳ ከተማ አካባቢ  ተጠልለው ከነበሩ 11 ሺህ ተፈናቃዮች ውስጥ 5 ሺህ 500ዎቹ ወደ የመጡበት የወረዳው ቀበሌዎች መመለሳቸውን ተናግረዋል ።

"ሌሎች ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ የአዝመራ ወቅት ከመድረሱ በፊት በፍጥነት ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና እራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው በፌዴራልና በሁለቱ ክልሎች ትብብር ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሰራዎች ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ መከናወናቸውን ተናግረዋል ።

በሁለቱም ዞኖች ካሉ ተፈናቃዮች ጋር በተደረገ ውይይት ወደ ቀድሞ ቀያቸው ተመልሰው የመኖር ፍላጎት እንዳላቸው ከተረጋገጠና መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ ስራው መከናወኑን አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል  ውሀ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተፈናቃዮች በሚመለሱባቸው የምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ አስር ቀበሌዎች ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ከቅድመ ዝግጅቱ በኋላ በተዘጋጀ ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሀ ግብር የተፈናቃይ ተወካዮች በቀበሌዎቹ ተገኝተው እንዲጎበኙ መደረጉን አመልክተዋል።

በቀርጫ ወረዳ 18 ቀበሌዎች በቀጣይ ምዕራፎች ተፈናቃዮን ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

እንደ አቶ አንተነህ ገለጻ የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አለመሆኑንና የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ባለመሆኑ ሊስተካከል መይገባል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራር አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ሰፊ የውይይት መድረክ መካሄዱን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የአካባቢው ማህበረሰብ አቀባበል በማድረግ ቤታቸውን በመስራትና በማስተካከል እንዲተባበሯቸው መግባባት ላይ መደረሱንም አስረድተዋል::

እንደ ዶክተር ደረጀ ገለጻ የፀጥታ ሁኔታውን አስተማማኝ ለማድረግ ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው የዘርፉ መዋቅር በቅንጅት እየሰራ ነው ።

በምክክር መድረኩ ተፈናቃቶችን በማቋቋም ዙሪያ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመው የቀጣይ የስራ እቅድ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም