የግእዝ ጉባዔ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀመረ

137
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 አራተኛው አገር አቀፍ የግእዝ ጉባዔ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀመረ። የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት ጉባዔ የቤተ ክህነት ሊቃውንት፣ የፌዴራልና የክልል ባሕልና ቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና እንግዶች በተገኙበት ዛሬ መካሄድ ጀምሯል። "የግእዝ ሃብት ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬና ነገ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ በግእዝ ቋንቋ አገራዊ ፋይዳ ላይ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይደረጋል። ጉባዔውን የከፈቱት የብሔራዊ  ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጮሻ፤ 'የግእዝ ቋንቋ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ የተሰነደበት፣ ከጥንት ጀምሮ የአገሪቱንና የቤተክርስቲያን ፍልስፍና፣ ጥበብና እውቀት ወደ ትውልድ  እንዲተላለፍ ያስቻለ ነው' ብለዋል። ግእዝ ቋንቋ የስነ ጽሑፍ ሐብት እንዲያድግና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ ለአማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጊኛና መሰል የአገሪቱ ቋንቋዎች የጽሕፈት መሰረት የሆነ ትልቅ አገር በቀል ቋንቋ እንደሆነ አቶ አብርሃም ገልጸዋል። የግእዝ ቋንቋ የቅኔ፣ የባሕል መድኃኒት፣ የፍልስፍና፣ የስነ ፈለክ፣ የስነ ስዕል፣ የቁጥር ስሌት፣ የስነ ምግባርና ስነ መለኮት ሀብቶች ተቀርጸው የተላለፉበት በመሆኑ ወደ ቀደመ ክብሩና ሚናው መመለስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ግዕዝ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች ጨምሮ ሌሎች የሥነ ጽሁፍ ሥራዎች የተሰነዱበት በመሆኑ በቋንቋው ላይ በጥናትና ምርምር የታገዘ ተግባር ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ዩኒቨርሲቲው በአገር በቀል ዕውቀቶች ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል። አራተኛው የግዕዝ ጉባዔ መዘጋጀቱ የአገር በቀል ዕውቀትና ሀብቶችን የማዳኛ ተልዕኮው አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። ለቁጥር የሚያዳግቱ አያሌ ድርሳናትና ምስጢራት የተከተቡበትን የግዕዝ ቋንቋ ለማዳንና ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም የተዘጋጁትን አገር አቀፍ የግእዝ  ጉባኤ  አክሱም፣ ባሕር ዳርና ጅማ በቅደም ተከተል ያለፉትን ጉባኤዎች አዘጋጅተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም