በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ቀን በመጪው ሐምሌ ይከበራል

147

ሚያዝያ 23/2011 በመጪው ሐምሌ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር አፍሪካዊያን ዲያስፖራዎችን የሚያቀራርብ "ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ" እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳስታወቀው ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሽንግተን ዲሲ የሚከበረው የኢትዮጵያ ቀን 'አብሮነት መሻል ነው' በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር አፍሪካዊያን ዲያስፖራዎች ተሳታፊ ይሆኑበታል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሐምሌ በሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞች በነበራቸው ቆይታ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር ሐምሌ 28 በየዓመቱ 'የኢትዮጵያ ቀን' ተብሎ በዋሽንግተን ዲሲ እንዲከበር የከተማው አስተዳደር መወሰኑ ይታወሳል። 

በዚሁ መሰረት 'ኖቫ ኮኔክሽንስ' የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ቀኑን አስመልክቶ በዋሽንግተን ዲሲ 'ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ' በሚል በየአመቱ የሚካሄድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በመጪው ሐምሌ 21 ቀን 2019 እንደሚካሄድ ለኢዜአ በሰጠው መረጃ አስታውቃል። 

የሚካሄደውን ዝግጅት አስመልክቶ ትናንት ምሽት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። 

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ፤ ዝግጅቱ ኢትዮጵያን ከሌሎች አፍሪካዊያን ወገኖቻቸው ጋር በጋራ ዕለቱን የሚያከብሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዝግጅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ የጀመሩትን ቀጣናዊ ትስስር የማጠናከር ጥረት የሚደግፍና ትውልደ አፍሪካዊያንን በይበልጥ ለማቀራረብ የሚያግዝ መሆኑን አምባሳደር ፍፁም ገልፀዋል።

ዝግጅቱ ከአንድ ቀን ሩጫ የዘለለ ፋይዳ እንዳለውና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ላይ የጎላ ሚና እንደተጫወተች ሁሉ በዚህ ዝግጅትም ከሌሎች አፍሪካዊያን ወገኖች ጋር በመሆን "አብሮነት መሻል ነው" በሚል መርህ ‘የኢትዮጵያ ቀን በዋሽንግተን ዲሲ' እንደሚከበር ተናግረዋል።

የውድድሩ ዋና አዘጋጅ የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጋሻው አብዛ፤ በመጪው ሐምሌ በዋሽንግተን ዲሲ የሚከበረውን የኢትዮጵያዊያን ቀን በየዓመቱ ለማክበር በርካታዎችን የሚያሳትፍ የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ዝግጅቱ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችን በበዓሉ ለማገናኘት የስፖርት እና የተለያዩ የባህል ፌስቲቫሎች ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑ ስለታመነበት ውድድሩ መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል። 

በርካታ ኢትዮያዊያን በሚኖሩበት ዋሽንግተን ዲሲ ባለፈው ሐምሌ 25 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ለመልካም ሀሳብ በፍቅርና አንድነት የተመካከሩበትን ወቅት የሚያስታውስ እና ትውልደ አፍሪካዊያንን ለማቀራረብ የሚረዳ ዝግጅት መሆኑን አመልክተዋል።

በዝግጅቱ ከሩጫው ጎን ለጎን ለሚኖሩበት ማህበረሰብና ለትውልድ አገራችው የጎላ አስተዋፅ ያደረጉ ዲያስፖራዎች ሽልማት የሚበረከትበት መድረክ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዋሽንግተን የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ዋና ተጠሪ ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ በበኩላችው፤ የሩጫ ውድድርን እንደመድረክ ተጠቅሞ የአፍሪካዊያኖችን ግንኙነት ማጠናከር የአትሌቶችንን ጥረትና ድካም ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

ዝግጅቱ የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 ያስቀመጠውን ዲያስፖራው በአፍሪካ የሚኖረውን  ተሳትፎ የማሳደግ ጥረት አካል መሆኑንም ገልፀዋል።

በውድድሩ ታዋቂ የአፍሪካ አትሌቶች፣ ሙዚቀኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የኃይማኖት መሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የሚሳተፉ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለውድድሩ ምዝገባ መጀመሩ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም