አለአግባብ የሚወገድ የፕላስቲክ ቆሻሻ በግብርና ሰራቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው በአክሱም አካባቢ አርሶ አደሮች ገለጹ

70

ሚያዝያ 23/2011 ከአክሱም ከተማ የሚወገድ የፕላስቲክ ቆሻሻ በግብርና ሰራቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው በአካባቢው አስተያየታቸው ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገለፁ።

ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

በከተማው ዙሪያ በሚገኙ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች እንዳሉት  ከተማ ተሰብሰቦ የሚወገድ ደረቅ ቆሻሻ በእርሻ ማሳዎችና በቤት እንሰሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ።

የዓዲ ክልተ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ኪዳነ ማሪያም ውብሸት  ከከተማው የሚሰበሰብ ደረቅ ቆሻሻ በእርሻ ማሳዎችና በግጦሽ ሜዳዎች አካባቢ እንደሚጣል ተናግረዋል።

በተለይ አካባቢውን በስፋት እየበከለ ያለው የፕላስቲክ ቆሻሻ እንሰሳት ስለሚመገቡት ለሞት እየዳረጋቸው መሆኑን ጠቁመዋል ።

"በቅርቡ በ10 ሺህ ብር የገዛኋት የወተት ላም ፕላስቲኩን በመመገቧ የአንድ ወር ጥጃት ትታ ሞታለች" ሲሉ ጠቅሰዋል ።

የዱራ ቀበሌ ነዋሪ ሓጂ አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው በ15 ሺህ ብር የገዙት የእርሻ በሬ የወዳደቀ ፕላስቲክ በመመገቡ መሞቱን ተናግረዋል ።

"ለእርሻ ያገለግለኛል ብዬ ያሳደኩት ወይፈን በበላው ላስቲክ ሆዱ ተነፍቶ ሞቷል"ያሉት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ደበሳይ ጌታቸው ናቸው ።

ወይፈኑ በተደረገለት የቀዶ ህክምና በሆዱ የተጠራቀመ ፕላስቲክ እንዲወገድ ቢደረግም ከሞት ሊተርፍ እንዳልቻለ አመላክተዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የላእላይ ማይጨው ወረዳ የእንስሳት ክሊኒክ አስተባባሪ አቶ ገብረመድሀን አለማየሁ በአካባቢው የሚወገድ ደረቅ ቆሻሻ በእንስሳት ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ለአርሶ አደሮች የቅሬታ ምንጭ መሆኑን ገልፀዋል ።

"ለዕቃ መያዥያነት እያገለገለ ያለው ስሰ ፕላስቲክ የጨው ጣዕም ሰላለው እንስሳት ይመገቡታል" ያሉት አስተባባሪው ፕላስቲኩ የእንስሳትን ሆድ በመንፋትና የምግብ ፍላጎታቸውን በመቀነስ ለሞት እንደሚዳርጋቸው አስረድተዋል ።

ፕላስቲክ በመመገብ በሚደርስባቸው የጤና እክል ወደ ተቋማቸው የሚመጡ የቤት እንስሳት በርካታ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

"አብዛኛዎቹ እንሰሳት የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ጤና ተቋሙ ስለሚመጡ ለሞት ይዳረጋሉ"ብለዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ የፕላስቲክ ቆሻሻው ለአካባቢ ብክለትም አይነተኛ ምክንያት ሆኗል ።

አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን አስረው በመቀለብ እንስሳቶቻቸውን ከጉዳቱ እንዲታደጉ መክረዋል ።

ከሁለት ሜትር በላይ ጥልቀትያለው ጉድጓድ በመቆፈር ፕላስቲኩን ማቃጠል ሌላው ጉዳቱን መታደጊያ መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአክሱም ከተማ የአረንጓዴ ልማት፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸሐዬ  በርሄ በበኩላቸው  "የደረቅ ቆሻሻ ማሶገጃ ጉድጓዱ የብረት አጥር እንዲሰራለት በመደረጉ ጉዳቱን ማስቀረት ተችሏል" ብለዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ።

ከከተማው በቀን 750 ሜትር ኩብ ደረቅ ቆሻሻ አንደሚወገድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም