የኦሎምፒክ ሳምንት በመጪው ሰኔ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል-የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

58

 አዲስ አበባ ሚያዝያ  23/2011 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ሳምንት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመጪው ሰኔ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገልጿል።

ይህ የኦሎምፒክ ቀን ''ኦሎምፒዝም ለሰው ልጆች ክብር ለሰላምና አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚከበረው።

ይህ ቀን ዝግጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን በዚህ ዓመትም ሰኔ 16 ቀን 2011 የሚከበር ይሆናል።

 በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀኑን አስመልክቶ  የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በማከናወን፣ በአውደ ርዕይ፣ በሙዚቃ ዝግጅቶችና ሌሎች ዝግጅቶችም ይከበራል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ይህን ቀን አስመልክቶ በሁሉም ከልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለአንድ ሳምንት በሚቆዩ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹት በዘንድሮው ዓመት የሚከበረው የኦሎምፒክ ሳምንት እንደከዚህ በፊቱ በአንድ የተመረጠ ከተማ ሳይሆን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ይህን ዝግጅት የክልል አመራሮች በበላይነት እንደሚመሩትም ነው የተናገሩት።

ይህ የኦሎምፒክ ሳምንት በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በኩል በመረጡት የስፖርት አይነት መከናወን እንደሚችልም ተነግሯል።

ይህ ዝግጅት በአዲስ አበባም የሚከበር ሲሆን በእግር ኳስ ፣ በአትሌቲክስ ስፖርት ውድድርና    ሲምፖዚየም በማዘጋጀት የሚከበር ይሆናልም ተብሏል።

ይህ ቀን ሲከበር የኢትዮጵያ ህዝብም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን በገንዘብ የሚደግፉበትን አሰራር እየዘረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ  ኮሚቴ  3 ሚሊዮን ያህል ሰዎች አባል እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነም ገልጿል።

አባሎችም በገንዘብና በሀሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ ይሆናልም ተብሏል። 

ዜጎች በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሲሆኑም የተቋሙን የገንዘብ አቅም በማጠናከር አትሌቶች በቂ የቅድመ ዝግጀት ጊዜ እንዲኖራቸውና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሀገራቸውን ወክለው ለሚሳተፉና ጥሩ ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ም ጠቀም ያለ ሽልማት ለመስጠትም ያግዛል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም