በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች የተሰጣቸውን መሬት በአግባቡ ያላለሙ 24 ባለሀብቶች ውላቸው ተቋረጠ

67
ጎንደር ግንቦት 28/2010 በማእከላዊና በምእራብ ጎንደር ዞኖች ለግብርና ኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን መሬት በአግባቡ ያላለሙ 24 ባለሀብቶች ውላቸው እንዲቋረጥ ማድረጉን የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታወቀ፡፡ ባለሀብቶቹ በገቡት ውል መሰረት በአግባቡ ያላለሙት 2ሺ 626 ሄክታር የእርሻ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የሰሊጥ ልማትና ግብይት የኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ ትናንት ሲጠናቀቅ በቢሮው የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የባለሀብቶቹ ውል የተቋረጠው በዚህ አመት ነው፡፡ የባለሀብቶቹ ውል እንዲቋረጥ የተወሰነው በገቡት ውል መሰረት የተረከቡትን የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት ለረጅም አመታት ሳያለሙ ጦም በማሳደራቸውና ለሶስተኛ ወገን በማከራየት ያልተገባ ጥቅም ማግኘታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ነው፡፡ ''ውላቸው የተቋረጠው ባለሀብቶች በሁለቱ ዞኖች በሚገኙ በመተማ፣ ቋራ፣ ጠገዴና ምእራብ አርማጭሆ ወረዳዎች በሰሊጥና ጥጥ ልማት ለመሰማራት ከቢሮው የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው የቆዩ ናቸው'' ብለዋል፡፡ ባላሀብቶቹ ላለፉት አምስት አመታት ሳያለሙ ጦም ያሳደሩትና ለሶስተኛ ወገን በማስተላለፍ አከራይተው ሲጠቀሙበት የቆዩትን 2ሺ 626 ሄክታር የእርሻ መሬት ውላቸው ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መወሰኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች 241 ባላሀብቶች ደግሞ ባሳዩት የአፈጻጸም ድክመት በቀጣይ እንዲያሻሽሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቢሮው በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የልማት አፈጻጸም የውጤት መገምገሚያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት በዚህ አመት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ የመገምገሚያ መስፈርቶቹም የባለሀብቶቹ ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ ተቋማዊ አደረጃጀታቸውና በሰለጠኑ ባለሙያዎች መመራታቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ባለፉት 9 ወራትም ቢሮው በመስፈርቱ መሰረት ባካሄደው የግምገማ ውጤት አሰጣጥ መሰረት በሁለቱ ዞኖች በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩ 1ሺ 154  ባላሀብቶች መካከል ለ948 የግምገማ ውጤት ሰጥቷል፡፡ በውጤቱ መሰረት ከፍተኛ የአፈጻጸም ደረጃ የተሰጠው ባለሀብት አንድ ብቻ ሲሆን መካከለኛ 758 ዝቅተኛ ውጤት ያገኙት ደግሞ 194 መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በምእራብ ጎንደር ዞን ምእራብ አርማጭሆ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ሙሉአለም ምልምሌ በተሰጠው ነጥብ መካከለኛ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረው ከውጤት መመዘኛዎቹ መካከል ሊሻሻሉ የሚገባቸው እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ ''በተለይ የ30 በመቶ ነጥብ የተሰጠው የማዳበሪያ አጠቃቀም ፍትሃዊ አይደለም'' ያሉት አቶ ሙሉአለም መሻሻል ይኖርበታል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ''የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በበቂ ማሟላት እንደ አንድ የመገምገሚያ ነጥብ መቀመጡ አግባብነት የለውም'' ያሉት በመተማ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ መልካሙ አብረሃም ናቸው፡፡ ባለሀብቱ ዘመናዊ የግብርና መካናይዜሽን የመጠቀም ፍላጎት ቢኖራቸውም በቂ የብድር አቅርቦትና ከቀረጥ ነጻ የግብርና መሳሪያዎችን ለማስገባት የተመቻቸ ሁኔታ በሌለበት መስፈርት ሆኖ መቀመጡ መካከለኛ ውጤት እንዳሰጣቸው ገልፀዋል፡፡ በክልሉ ከፍተኛ ሰሊጥ አብቃይ በሆኑት በምእራብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች 1ሺ 154 ባለሀብቶች በ134ሺ 218 ሄክታር መሬት በሰሊጥና ጥጥ ልማት ተሰማርተው እንደሚገኙ ቢሮው አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም