የሶማሌና ኦሮሞ ህዝቦችን ይበልጥ በማቀራረብ ለሰላም በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል

90

ሚያዝያ22/2011 ዓ.ም የሶማሌና ኦሮሞ ህዝቦችን ይብልጥ በማቀራረብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በአዳማ ከተማ ነገ ለሚካሄደው የሁለቱ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ የሶማሌ ክልል ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገብተዋል።


የሶማሌ ክልል የልኡካን ቡድን መሪና የአገር ሸማግሌ መሪ ገራድ ኩልሚዬ እንደገለጹት ከዚህ በፊት በነበሩ አመራሮች በሁለቱ ህዝቦች ላይ መጉላላትና ብዙ መፈናቀል ተከስቷል።


በነገው እለት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የሚደረገው ውይይትም ችግሮችን በንግግር ለመፍታትና በቀጣይ መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ይብልጥ በመቀራረብ ለመስራት ነው ብለዋል።


የሶማሌና የኦሮሞ ህዝቦች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኬንያ፣በሶማሊያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰው የሁለቱን ህዝቦች ማቀራረብና አንድነታቸውን ማጎልበት ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ መሆኑንም አስርድተዋል።


የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው በነገው እለት በኣዳማ የሚካሄደው የህዝብ ለህዝብ መድረክ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች በማቀራረብ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የሶማሌና የኦሮሞ ህዝቦች በቋንቋ፣በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን በደምና በስጋም ጭምር የተዋሃዱ እንዲሁም በደል ሲደርስባቸው በጋራ በመቆም መሰዋትነት የከፈሉ ናቸው ብለዋል።

ከዚህ በፊት የተከሰቱት ችግሮች ጥቅማቸው የቀረባቸው አካላት የፈጠሩት መሆኑን አስታውሰው የነገው ጉባዔ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ችግሮች ዳግም እንደይከሰቱ የጋራ መግባባት ይደረስበታል ብለዋል።

ደግመው እንዳይከሰቱ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ወጣቶችና ከምሁራን ጋር የተጀመሩት ነገሮች ወጥ በሆነ መልኩ ለመስራት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።


በጉባዔው ላይ ከ2 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 500ዎቹ ከሱማሌ ክልል የመጡ ተሳታፊዎች መሆኗቸው ታውቋለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም