በማእከላዊ ጎንደር በዘመቻ ከ15ሺ በላይ ለሚሆኑ ህጻናትና ታዳጊዎች ክትባት ተሰጠ

144

ጎንደር ሚያዚያ 22/2011 በማእከላዊ ጎንደር በተፈናቃዮች መጠለያዎች የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል ከ15ሺህ በላይ ህጻናትና ታዳጊዎች ክትባት መሰጠቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመጠለያዎቹ የጤና ችግር የገጠማቸው 20ሺህ ለሚጠጉ ተፈናቃዮችም ነጻ የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመምሪያው የኅብረተሰብ የጤና አደጋ ምላሽ ሰጪና ማቋቋም ኦፊሰር አቶ ተምሮ አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ክትባቱ የተሰጠው በአራት መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ህጻናትና ታዳጊ ወጣቶች ነው፡፡

በትክል ድንጋይ መጠለያ ጣቢያ በአራት ህጻናት ላይ የተከሰተው ኩፍኝ ወደ ወረርሽኝ እንዳይቀየር ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የክትባት ዘመቻ ህጻናቱን ከበሽታው መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለህጻናቱ በተጨማሪም የቫይታሚን ኤ፤ የአንጀት ጥገኛ ትላትል እንክብል መድኃኒት እደላና በተመጣጠነ ምግብ እጦት የጤና ችግር ለገጠማቸው ህጻናትም የህክምናና የአልሚ ምግብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ 11 ጊዚያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ 20ሺ ለሚጠጉ ተፈናቃዮችም በተቋቋሙ ጊዚያዊ ክሊኒኮች አማካኝነት ከማናቸውም ክፍያ ነጻ የሆነ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም 3ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች የገጠማቸውን የእከክ በሽታ የጤና ችግር ለማቃለልም ነጻ ህክምና መሰጠቱን ኦፊሰሩ ተናግረዋል፡፡

መምሪያው ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት በመጠለያዎቹ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የቲቢ በሽታ ልየታን ጨምሮ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ታማሚዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ለተፈናቃዮቹ በተሰጠው የመድሃኒትና የላቦራቶር አገልግሎትም መንግስት ከ150ሺ ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

“ወደ መጠለያው በገባንበት ወራቶች ህክምና ለማግኘት ችግር ገጥሞን ነበር አሁን ላይ በመጠለያው በተቋቋመው ጊዚያዊ ክሊኒክ ነጻ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት በቅተናል” ያሉት በትክል ድንጋይ መጠለያ የሚገኙት አቶ አስረስ ታከለ ናቸው፡፡

“የአምስት አመት ልጄን ይዤ በአይምባ መጠለያ ከገባሁ አራት ወር ሞልቶኛል” የሚሉት ወይዘሮ ሞሚና ሰይድ በመጠለያው በተሰጠው የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ልጄን ማስከተብ ችያለሁ ብለዋል፡፡

በማእከላዊ ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ59ሺህ በላይ አባወራና ቤተሰቦቻቸው በጊዜያዊ መጠለያዎችና ከቤተሰብ ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ መገለጹ ይታወሳል፡፡