የዓለም የፕሬስ ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል

73

አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2011 የዓለም የፕሬስ ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ ለኢዜአ እንዳሉት የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ከተለያዩ የአለም አገሮች ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነትያላቸው ሙያተኞች ከነገ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

በነገው እለት የክልልና የፌዴራል የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ ውይይት ይካሄዳል።

በዚህም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ያሉበት ደረጃ ከስነ ምግባርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይዳሰሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

በመድረኩ አዳዲስ የዘርፉ ሙያተኞች፣ በዘርፉ ልምድ ያላቸውና አንጋፋ ባለሙያዎች ተገኝተው በችግሮችና መፍትሄዎቻችው ላይ ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዝሃን ችግሮቻቸው ላይ በመምከር በቀጣይ የተሻለ መስራት የሚያስችሉ ሃሳቦችና መፍትሄዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ነገ ከሚደረገው አገር አቀፍ ውይይት ቀጥሎም ዓለም አቀፍ ውይይቱ በተያዘለት መርሃ ግብር እንደሚከናወን ታውቋል።

ከተለያዩ የዓለም አገሮች ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነትያላቸው ሙያተኞችም ከነገ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ዝግጅቱን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪ ከዩኒስኮ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

ኢትዮጵያ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞችንና አክቲቪስቶችን በመፍታትና በመረጃ ነጻነት ላይ ያሳየችውን መልካም ጅምር ለማበረተታት የዘንድሮው የፕረስ ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር ዩኔስኮ መወሰኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም