የማምቡክን ግጭት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው ገብቷል ተባለ

106

አሶሳ ሚያዚያ 21/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳንጉር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት የሚያጣራ የተደራጀ የምርመራ ቡድን ዛሬ ወደ አካባቢው መግባቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ።

የአማራ ክልል በበኩሉ በአካባቢው የተከሰተውን ችግር በጋራ ለመፍታት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ግጭት የተከሰተበት የዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማና አካባቢው በፌደራልና ክልል የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

ግጭቱ የተከሰተበት አካባቢ ዛሬ ማምሻውን እየተረጋጋ መሆኑን አመልክተዋል።

"ዛሬ ረፋዱ ላይ የተደራጀ የክልሉ የምርመራ ቡድን ወደ አካባቢው ገብቷል" ብለዋል።

በሌሎች አንዳንድ የወረዳው ቀበሌዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ተመሳሳይ ግጭት መከሰቱን ጠቁመው በዚህም ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን እና የወደመውን ንብረት ትክክለኛ መጠን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

ነገ  የጉዳቱን ትክክለኛ መጠን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ እንደሚያደርጉ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

ከግጭቱ ጀርባ አንዳንድ የአካባቢው አመራሮች እጃቸው እንዳለበት ነዋሪው እየገለጸ ስለመሆኑ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ አሁን በጉዳዩ በቂ መረጃ ስለሌላቸው ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አስረድተዋል፡፡

"የምርመራውን ውጤት መሠረት በማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በወንጀሉ የተሳተፉትን የክልሉ መንግስት ለህግ ያቀርባል"ብለዋል፡፡

" ከክልሉ አንድም ሰው እንዲፈናቀል አንፈልግም"ያሉት አቶ አሻድሊ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡ አካባቢውን ለቆ እንዳይወጣ የጸጥታ ጥበቃውን በማጠናከር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

"በጉዳዩ ላይ ከጎረቤት የአማራ ክልል ጋር በቅርበት እየተነጋገርን ነው” ያሉት አቶ አሻድሊ የማረጋጋት ሥራውን በጋራ ለማከናወን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አሶሳ እየመጡ  መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አሻድሊ የክልሉ መንግስት በግጭቱ በጠፋው የሰው ህይወት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው ገልጸው ለቤተሰቦቻውም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል  በአካባቢው የተከሰተውን ችግር በጋራ ለመፍታት  ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰማሃኝ አስረስ ለኢዜአ እንደገለፁት በዳንጉር ወረዳ  ሰሞኑን በሁለት ጫኚ አውራጅ ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በተነሳ ግጭት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ  ጉዳት ደርሷል፡፡

በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት ክልሉ የተሰማውን ሀዘን መግለጹን አስታውቀዋል። 

"የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ግጭት የብሄር መልክ እንዲይዝ የሚጥሩ አካላት አሉ ” ያሉት ኃላፊው ግጭቱን የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ገብተው በመረጋጋት አሁን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡

 አቶ አሰማሃኝ "በሁለቱ ክልል ህዝብና መንግስት ምንም ዓይነት ችግር የለም " ብለዋል።

የሁለቱ ክልል መንግስታት ዜጎችን ከጉዳት ለመጠበቅና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤በቀጣይም መሰል ችግር እንዳይከሰት ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ስራዎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል፡፡

በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ አድጎ አምሳያ ማሳወቃቸውን ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር 15 መድረሱም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም