በህገወጥ ደላሎች ተታለው ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ 16 ወጣቶች ተያዙ

64

ሚያዚያ 21/2011 በደቡብ ወሎ ዞን የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፖሊስ ቁጥጥር የለም በሚል በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ አረብ ሃገር ለመውጣት የሞከሩ 16ወጣቶች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ወጣቶቹን በህገ ወጥመንገድ ለማስወጣት የሞከረው አንድ ደላላም ተይዟል፡

የቃሉ ወረዳ ፖሊስ  ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ስራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር ይመር አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተያዙት ሚያዚያ 20/2011ዓ.ም ነው።

በህገ ወጥ ደላሎች ተታለው ከአጎራባች ዞኖች በመሰባሰብ በአፋር በኩል  ወደ አረብ ሀገር ለመሻገር ሲሞክሩ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆመ በደጋን ከተማ ተይዘዋል፡፡

በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የተገኙት ወጣቶቹ አረብ ሀገር ሲደርሱም እያንዳንዳቸው 30 ሺህ ብር ሊከፍሉ ተስማምተው ጉዞ መጀመራቸውን ለፖሊስ በሰጡት ቃል መረጋገጡን ምክትል ኮማንደሩ አስረድተዋል፡፡

ግለሰቦቹ በደላሎች አማካኝነት ከሰሜን ሸዋ፣  ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞኖች ተሰባስበው ከኮምቦልቻ ከተማ የተነሱ ሲሆን እድሜያቸውም ከ15 እስከ 20 ዓመት  ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

ምክትል ኮማንደር ይመር እንዳሉት የጉዟቸዉ መነሻም ሰሞኑን የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የፖሊስ ቁጥጥር እንደሌለና የመን ላይም መንገዱ ክፍት ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ ስለሰጧቸው ነው።

ከተለያዩ ሀገራት ደላሎችጋር በመነጋገር ወጣቶችን ያቀባብላል ተብሎ የተጠረጠረ አንድ ግለሰብም ከወጣቶች ጋር ተይዞ ጉዳዩን  ፖሊስ እያጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በቃሉ ወረዳ ደጋንናገርባን ከተሞች ላይ በየቀኑ በአማካኝ ከአምስት ያላነሱ ሰዎች እንደሚያዙ አመልክተው  በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ኑሯቸውን የመሰረቱ ህገ ወጥ ዳላሎች በመኖራቸው ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተያዙት ወጣቶች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው  እንዲመለሱ የሚደረግ መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ አረጋግጠዋል።

በቃሉ ወረዳ በተያዘው ወር ብቻ  የአሁኖቹን ሳይጨምር ከ50 በላይ ወጣቶች በህገወጥ መንገድ ወደ አረብ ሀገር ሊወጡ ሲሞክሩ መያዛቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም