ኢትዮጵያ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር 4 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት ስምምነቶችን አድርጋለች

108

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2011ኢትዮጵያ በቻይና በተደረገው የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ 4 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት የሚያስገኙ ስምምነቶችን ማድረጓ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከጉባኤው ጎን ለጎን ትልልቅ የኢንቨስትመንት መጠን ያላቸው ስምምነቶች ተደርገዋል።

በዚህም ከ5 የተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች በዋነኛነት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ካላት ፍላጎት አንጻር ከፍተኛ አቅምና የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚፈጥሩ ናቸውም ተብሏል።

ስምምነቶቹ በሃይል አቅርቦትና ማከፋፈል፣ በፐልፕና ወረቀት ማምረት፣ በህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ማምረት፣ በስጋ ማቀነባባሪያ እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተደረጉ እንደሆኑም ገልጸዋል ኮሚሽነሩ።

እነዚህ ስምምነቶች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሲሆኑ በ2010 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ከነበረው የ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ስምምነቶች በበለጠ በዚህ በጉባኤው ጎን ለጎን ብቻ የተደረጉት ስምምነቶች 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኙ ናቸው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት እስቴት ግሪድ ኮርፖሬሽን ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር  የኢንቨስትመንት መጠን ያለው ሲሆን ለ16 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃይል አቅርቦትና ስርጭት ያቀርባል።

በዚህም ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ያልተቆራረጠ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር በማገዝ ለባለሃብቶች  አቅምን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ለተመረጡ ከተሞችና ለአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ተጨማሪ የሃይል አቅርቦት ያቀርባል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘውን ሰፊ የቀርከሃ ምርት ለመጠቀም 2 ቢሊዮን ዶላር  ኢንቨስትመንት መጠን ያለው ታይሰን ግሩፕና ግሪን ዳይመድ የተባሉ ኩባንያዎች በጥምረት በአሶሳ ከተማ ፐልፕና ወረቀት የማምረት ኢንቨስትመንት ሌላኛው ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ ከወረቀት የወጭ  ንግድ ገቢ እንድታገኝ በማድረግና ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ማምረቻ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት የተስማማው ዣንደይ ሜዲካል የተሰኘ የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ አምራች በ75 ሚለዮን ዶላር  የኢንቨስትመንት መጠን በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት ያደርጋል ተብሏል።

ኢንቨስትመንቱ በአሁኑ ወቅት በብዛት ከውጭ እየገባ ያለውን የመድሃኒት እና ህክምና ቁሳቁስ ወጪ በመቀነስ አንደሚያግዝም አብራርተዋል።

በቻይና ትልቅ ከሚባሉ የህትመት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ኤቢቲ ፕሪንቲንግ እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያ ምዕራፍ ኢንቨስት የሚያደርግ ሲሆን በዚህም ኢትዮጵያ ለህትመት እያወጣች ያለውን ወጪ በመቀነስና ለጎረቤት አገሮች የህትመት አገልግሎት በመስጠት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቡና  ምርትን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ስምምነትም ተደርጓል።

ሌላኛው በኢትዮጵያ በግንባታና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተሳተፈ የሚገኘው ሲ.ጂ.ሲ.ኦ.ሲ የተሰኘ ቡድንም በአዋሽ ፈንታሌ እስከ 215 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ኢንቨስት በማድረግ በስጋ ማቀነባበሪያ ለመሰማራት ስምምነት አድርጓል።

ኢንቨስትመንቱ በአካባቢው ያለውን የእንስሳት ሃብት ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ የውጭ ንግድን በማበረታታትና ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ አድል በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ይሆናል።

ይህ ኩባንያ በዓመት የ300 ሺህ የቀንድ ከብትና የ3 ሚሊዮን በጎችን እርድ አቀነባብሮ ለገበያ እንደሚያቀርብም ይጠበቃል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድን የተሳተፈበት ሁለተኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 26 እና 27 መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ውይይቶች ውጤታማ እንደነበሩ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም