የኢትዮ - ሱዳንን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል ተባለ

69

ሚያዝያ 21/2011 የኢትዮጵያና ሱዳንን የኢኮኖሚ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮ- ሱዳን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ሁለቱ ሀገሮች በሰፊ ድንበር የሚገናኙ፣ በባህል፣ በታሪክና በሁለትዮሽ ትብብር ቢኖራቸውም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስራቸው ከሚጠበቀው በታች ነው ተብሏል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እንዳሉት፤ ሁለቱ ሀገሮች የዳበረ የባህል፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር አላቸው።

በመሆኑም በሱዳን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ባለው ሁለንተናዊ ትብብር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖረውም ብለዋል።

በአፍሪካ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሁለቱ ሀገሮች ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሱዳን ባለሃብቶች ማህበር ፕሬዘዳንት አላጂድ አብዱልከሪም ሰይድ የሱዳን የፖለቲካ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት አያሻክርም ብለዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በፖለቲከኞች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ለዓመታት የተገነባ ወንድማማችነት ነው ብለዋል።

የሱዳን መንግስት ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለልማትና ለጋራ ትብብር የሚሰራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ አዲሱ አስተዳደር በሁለቱ ሀገሮች የሁለትዮሽ ትብብር ላይ የሚስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም ብለዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን የተቀዛቀዘውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮ- ሱዳን የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ካርቱም የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲና አዲስ አበባ በሚገኘው የሱዳን ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ከ100 በላይ ታዋቂ የሱዳን ናየአትዮጵያ ባለሀብቶችና የኩባንያ ሃላፊዎች ተሳትፈውበታል።

የፎረሙ ተሳታፊዎች በነገው እለት በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያቸውን ከሚያፈሱት ከቻይና፣ ህንድና ቱርክ ቀጥሉ ሱዳን አራተኛ ደረጃ ላይ አንዳለች መረጃዎች ያሳያሉ።

እስካሁን ባለው መረጃ ከ 100 በላይ የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም