በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ11 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆኑ

59

ሚያዝያ21/2011በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ11 ሺህ 600 ወጣቶችን በማደራጀት  የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።

የዞኑ  ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ  ኃላፊ አቶ ተስፋየ ገብሬ ለኢዜአ እንዳሉት  የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑት  በበጀት ዓመቱ ለ19 ሺህ 300 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት  ከታቀደው ውስጥ ነው።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል 348 የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ናቸው።

ኮንስትራክሽን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎት እና ግብርና ወጣቶቹ ተደራጅተው የተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። 

ወደ ስራ ለገቡት ወጣቶች በተዘዋዋሪ ብድር ከ63 ሚሊየን ብር በላይ ብድር  እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

የተገነቡ 38 የመስሪያና መሸጫዎች ለአንቀሳቃሾች ማስተላለፍ ተችሏል፡፡

በቀሪ ወራት በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ የስራ ዘርፎች ወጣቶችን በማሰማራት እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከስራ ዕድሉ  ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ኬኔዲ ሸጋው እንደገለጸው በግንባታ  የስራ ዘርፍ አምስት ሆነው በመደራጀት ከህዳር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ጀምረዋል።

በ3 ሚሊየን ብር በጀት የጤና ባለሙያዎችን ማረፊያ ህንጻ ግንባታ በተቋራጭነት  ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

"የተማርንበትን የሙያ ዘርፍ መሰረት ተደርጎ የስራ እድል መፈጠሩ በሙያው ልምድ እንድናገኝ አድርጎናል"ያለው ወጣት ኬኔዲ በተሰማሩበት የግንባታ ዘርፍ የሚያገኙት ገቢ ሀብት ለማፍራት እንደሚያስችላቸው አመልክቷል፡፡

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው  ወጣት ሰለሞን ወርቁ በበኩሉ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በዶሮ እርባታ መሰማራታቸውን ገልጿል።

ወጣቱ እንዳለው ለስውው ማንቀሳቀሻ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

"በተመቻቸልን የስራ ዘርፍ ሰርቶ ለመለወጥና ሀብት ለማፍራት ትልቅ ተስፋ ይዘን እየሰራን ነው"ብሏል፡፡

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አሁንም ቀጥሎ እንዳለ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም