የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ በመባል ተሸለመ

118

ሚያዝያ 21/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ የ2019 የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ አገልግሎት ሽልማትን ተቀዳጀ።

ሽልማቱን ያዘጋጀው የኤር ካርጎ ኒውስ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርጎ ዜናዎችን በመዘገብ፣ የኢንዱስትሪውን መሪዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግና ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ ትንታኔዎችን በመስራትና ለአለም አቀፍ  የአየር ጭነት አገልግሎት ሰጪዎች ሪፖርቶችን በማዘጋጀት የታወቀ ነው።

በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የአየር ጭነት አገልግሎት አቅራቢው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽልማቱን ሚያዚያ 18 በእንግሊዝ ለንዴን ተቀብሏል።

“ቤስት ካርጎ ኤር ላይን 2019 “ተሸላሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ሽልማቶችን መቀዳጀቱንም ዘገባው አስታውሷል።

በኤር ካርጎ ኒውስ የሚዘጋጀው “የአመቱ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ “ የሚሰኘው ሽልማት በዘርፉ የተከበረና ከፍተኛ እውቅና ያለው ሽልማት ነው።

ሽልማቱን አስመልክቶ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረ ማርያም”ይህነን የተከበረ ሽልማት በመቀዳጀታችን ከፍ ያለ ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

ስኬቱ የጭነት አገልግሎታችንን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት የያዝነውን ቁርጠኝነትና የመደብነውን ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አገልግሎት ለአፍሪካና ለተቀረው አለም የማህበራዊ ኢኮኖሚ እድገት የሚጫወተውን ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው አገልግሎቱ ደህንነቱ የተጠበቀ፣አስተማማኝና ተወዳዳሪ መሆኑንም አስረድተዋል።

አየር መንገዱ እኤአ በ2025 ለማሳካት ካስቀመጣቸው ራዕዮቹ አንዱ የሆነውና በአመት 1 ሚሊዮን ቶን እቃ የመያዝ አቅም ያለውንና በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የካርጎ ተርሚናል አስገንብቶ ወደ ስራ ገብቷል።

የጭነት አገልግሎቱንም በአፍሪካ፣ የባህረ ሰላጤው አገራት፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ላቲን አሜሪካ እና አውሮፓ በሚገኙት የአየር መንገዱ  44 አለም አቀፍ መዳረሻዎች ይሰጣል።

አየር መንገዱ 11 ቦይንግ 777 ኤፍ እና 2  ቦይንግ 738 ኤፍ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በቀን 400 ቶን ጭነት ያጓጉዛል።

አየር መንገዱ የያዘውን አስደናቂ እድገት ተከተሎ የዘረጋው የጭነት አገልግሎት ኢንዱስትሪ መር የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር የአፍሪካ አገራትን የወጪና ገቢ ኢኮኖሚ እያሳደገው ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ በ2025 በጭነት አገልግሎት አመታዊ ገቢውን 2 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም