በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊከሰት ይችላል

91
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ። በቅርቡ በሲዳማና በቡታጅራ የመሬት መንሸራተት ተከስቶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና ትግራይ ከልሎች የመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ አደጋ ሊከሰት ይችላል የሚል ትንበያ አለ። ለዚህም በወቅቱ እየጣለ ያለው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ ምክንያት እንደሚሆን ገልጸዋል። ህብረተሰቡም በአካባቢው ያለውን የወንዝ ሙላት መጨመር በቅርብ በመከታተልና ከሚመለከተው አካል የሚሰጠውን የአየር ንብረት ትንበያ በመከታተል እራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ አሳስበዋል። ኮሚሽኑ ከዝናብ መጨመር ጋር ተያይዞ ለሚከሰት አደጋ ብሔራዊ የጎርፍ አደጋ  ግብረ ሃይል አቋቁሞ እየደረሰ ላለው አደጋ ምላሽ በመስጠትና የቅድመ ጥንቃቄ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም