የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

89

ሚያዝያ 19/2011 የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጀርመን በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው እንዳለፈ ዛሬ ተሰምቷል።

አስከሬኑ ከጀርመን ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ብሔራዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ለማካሄድ ኮሚቴ ይቋቋማል።

አስተባባሪ ኮሚቴው በሚያወጣው የስርዓተ ቀብር መርሃ ግብር አማካኝነት ቀብራቸው ይፈጸማል።

በነሐሴ ወር 1935 ዓ.ም በምዕራብ ኢትዮጵያ ደምቢዶሎ የተወለዱት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ላለፉት 30 ዓመታት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው።

ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።

ዶክተር ነጋሶ በማህበራዊ ታሪክ ከፍራንክፈርት አም-ሜይን ጎተ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።

ጀርመናዊቷን ነርስ ሬጂና አቤልት አግብተው በትዳር ኖረዋል።

ዶክተር ነጋሶ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት የሽግግር መንግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ (ኢህአዴግ) ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ነበሩ።

ዶክተር ነጋሶ የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ወራት ሲቀራቸው ከኦህዴድና ከኢህአዴግ ጋር ባለመግባባት ለቀው መውጣታቸው ይታወቃል።

በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በግል ተወዳዳሪነት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው በማሸነፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመግባት በቅተው ነበር።

በሐምሌ 2000 ዓ.ም የዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሲመሰረት መስራች አባል በመሆን በፓርቲው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም