በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማምቡክ ከተማ በደረሰው ግጭት የሟቾች ቁጥር 10 ደረሰ

83

አሶሳ ሚያዝያ 19 ቀን 201 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማምቡክ ከተማ በተከሰተው ግጭት የሟቾች ቁጥር 10 መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት እስከ ትናንት ሕይወታቸው ያለፈው ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ ሐመደኒል ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ደግሞ በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸው ፓዌ ሆስፒታል ሲታከሙ የነበሩ ሌሎች ስምንት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

እንዲሁም ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና በማግኘት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ግጭቱ የተከሰተው በእቃ ጫኝና አውራጅ መካከል በተፈጠረ የዋጋ አለመግባባት ሲሆን፣ የግለሰቦቹ ህይወት ያለፈው በግጭት ወቅት በዱላና በድንጋይ በመደብደባቸው ነው፡፡ 

ከግጭቱ ጋር የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ምርመራው መቀጠሉን ኮሚሽነር መሐመድ አስረድተዋል ፡፡

“በአሁኑ ወቅት በማምቡክ ከተማ ሰላም እየተመለሰ ነው'' ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ የትንሳዔን በዓል እንዲያከብር የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች የማረጋጋት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

''በግጭቱ እጁ ያለበት ማንኛውም ግለሰብ ለህግ ይቀርባል” ያሉት ኮሚሽነር መሐመድ፣ ኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

በቅርቡ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችንም ያሳተፈ ህዝባዊ ውይይት እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡

ማምቡክ የዳንጉር ወረዳ ርዕሰ ከተማ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም