በገዋኔ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ

64

ሰመራ ሚያዚያ 19/2011 በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ትናንት በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ከሎይታ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በእንድፍኦ ቀበሌ ልዩ ስሙ አንቡሌ በተባለ ቦታ በጦር መሳሪያ ታግዞ በተፈጸመ ጥቃት ነው።

ጥቃቱ የደረሰው ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በመጓዝ ላይ በነበሩ የትግራይ ዋልታ ስፖርት ቡድን አባላት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ግለሰቦች ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መላካቸውንም አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግሥት በጥቃቱ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ማዘኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

ጥቃቱን ያደረሱ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ ከአገር መከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥቃቱ በህዝቦች መካከል መጠራጠርንና መቃቃርን ለመፍጠር በሚፈልጉ አካላት የተቀነባበረ ሴራ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል።

ጥቃቱ የደረሰበት ቀበሌ  የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ የተቃጠለበትና የኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት አገልግሎት የተስተጓጎለበት አካባቢ እንደነበረም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም