በመተከል ዞን ማምቡክ ከተማ በተከሰተ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን ማምቡክ ከተማ በተከሰተ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ
41
ቤንሻንጉል ሚያዚያ 18/2011 በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ማምቡክ ከተማ በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ ሀመደኒል ማምሻውን ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት ማታ የተከሰተው ግጭት በሁለት እቃ ጫኚ አውራጅ ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ የጉልበት ስራ ዋጋ አለመግባባት ነው።
ከጉዳዩ ጋር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በትብብር አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
“ ህግ በሚከበርበት ሀገር ነው የምንኖረው” ያሉት ኮሚሽነር መሐመድ፤ የጸጥታ አካላት የህግ የበላይነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት አጥፊዎችን ለማጋለጥ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም ወጣቱ ከስሜታዊነት በመራቅ ግጭት ሲከሰት በሰከነ አኳኋን በህግ አግባብ ሊመራ እንደሚባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመተከል ዞን የዳንጉር ከተማ የሆነችው ማምቡክ 30ሺህ ያህል ህዝብ እንደሚኖርባት ይገመታል።