መገናኛ ብዙሃን የተፈጠረላቸውን ሙያዊ ነፃነት በኃላፊነት በመጠቀም በኩል ክፍተት ይታይባቸዋል- የዘርፉ ባለሙያዎች

68

ጎባ- ሚያዝያ 18/2011  መገናኛ ብዙሃን የተፈጠረላቸውን ሙያዊ ነፃነት መሰረት አድርገው  በኃላፊነት በመጠቀም በኩል ክፍተት እንደሚታይባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳሉት በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል።


በመዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት መምህር አቶ ጣሂር አብዱላሂ  በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጋዜጠኞች ነፃ ሆነው በመስራት ረገድ ችግር እንደነበረ  ተናግረዋል።

በተለይም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን  ተቋማት የሚመሩት ከሙያው ይልቅ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ  እሳቤዎችን ማስረፅ ላይ ቅድሚያ ሰጥተው ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው ይህም ተዓማኒነት እንዳይኖራቸውና ህብረተሰቡ ወደ ማህበራዊው ሚዲያ ፊቱን እንዲያዞር ማድረጉን አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከተጽእኖ ነጻ ሆነው እንደፈለጉ የሚዘግቡበት ምቹ ሁኔታ  ቢኖርም  የተፈጠረላቸውን የሙያ ነፃነት መሰረት አድረገው በመስራት በኩል ያለባቸው ክፍተት ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል።

"በአቅም ግንባታ ስልጠናና ተያያዥ ድጋፎችን በማድረግ ክፍተቶችን መሙላት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል "ብሏል፡፡
ሀገሪቱ የተሻለ ይዘት ያለው የመረጃ ነፃነት ህግ ቢኖራትም መረጃን ለዜጎች በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ የተናገረው ደግሞ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የባሌ ዞን  ጽህፈት ቤት አዘጋጅ አቶ አብዱረዛቅ መሐመድ ነው፡፡

"በሀገሪቱ በዘርፉ የወጡ ህጎች ችግር ባይኖርባቸውም አፈጻጸማቸው ላይ ክፍተት በመኖሩ ዜጎች መረጃን ለማግኘት ሌሎች አማራጮችን እንዲያዩ እያደረገ ነው" ብለዋል።

በተለይ እውነታን መሰረት ያለደረጉ ሚዛናቸውን ያልጠበቁ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ የተሳሳቱ  መረጃዎች አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ  መሆናቸውን በማሳያነት አቅርቧል፡፡

አቶ አብዱረዛቅ እንዳመለከተው መንግስት መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተከትለው እንዲሰሩ  ተከታታይነት ያለው ስልጠናና ድጋፍ ማድረግ አለበት።

በየደረጃው በተዋቀሩ የመንግስት አደራጃጀቶች መረጃን ለህዝቡ ክፍት በማድረግ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ላይ  በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

 በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት መምህር  አቶ በደዳ ያደታ በበኩላቸው በሃገሪቱ  በማረሚያ ቤቶች  የነበሩ ጋዜጠኞች በሙሉ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን እንደ መልካም ጅማሮ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ከልክ በላይ ከሆነ የመንግስት ወገንተኝነት ተላቀው የህዝቡን እሮሮ ማሰማት መጀመራቸው  የሚበረታታ ቢሆንም ሁሉንም አስተሳሰቦችን እኩል በማስተናገድና በኃላፊነት በመስራት በኩል ክፍቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ስራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ መከታ ሊሆንላቸው የሚችል ህግ ተግባራዊ ከማድረግ  ባሸገር ከሙያው ስነ ምግባር ውጪ የሚንቀሳቀሱትን የተጠያቂነት አግባብ እንዲኖር በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ  የፕሬስ ቀን ቀጣይ ሳምንት በኢትዮጵያ እንዲከበር  መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም