የትንሳኤው በዓል እርስ በእርስ በመከባበርና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል- በሀዋሳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች

117

ሀዋሳ ሚያዝያ 17/2011ዓ. የትንሳኤው በዓል እርስ በእርስ በመከባበር ፣ አንድነት በሚያጠናከርና ታላቅ ታናሹን ዝቅ ብሎ በመታዘዝ ማክበር እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ነዋሪዎች አመለከቱ።

በዓሉን እንደቀድሞው ከጎረቤቶቻቸውና ከችግረኞች ጋር አብረው እንደሚያከብሩም  ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ኢየሱስ  ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት በዓለ ሐሙስን በማስታወስ ህብረተሰቡ  በዓሉን ሲከብር ታላቅ ለታናሹ መታዘዝንና ማገልገልን በማሳየት ሊሆን  ይገባል።

በከተማው ታቦር ክፍለ ከተማ የሆገኔ ዋጮ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት በላይ በሰጡት አስተያየት"  አለምን ለማዳን የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበው ታላቅ ታናሹን ማክበር እንደሚገባው ለእኛ ለማስተማር ነው" ብለዋል።

ለረጅም ዓመታት በፍቅር ፣በመቻቻልና በአንድነት ተሳስቦ አብሮ የመኖር ባህልን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተሸረሸረ እንደመጣ ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዋ እንዳመለከቱት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ እየተስተዋለ ያለው ነገር አንድነትን የሚያጠፋና ሰው እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያይ የሚያደርግ ነው።

"ይህን ሁኔታ ለመቀየር ዛሬ የሚያስፈልገን ፍቅርና ሰላም ነው ፤ይህን ለማምጣትም እርስ በእርስ መከባበር፣ መረዳዳት እና ታላቅ ታናሹን በማገልገል ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

በሀዋሳ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የፊላደልፊያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ  ትርንጎ ታምራት በበኩላቸው በጋራ የመኖርና የመተጋገዝ ልምድ እየቀረ መምጣቱን ገልጸዋል።

" የፋሲካን በዓል ከጎረቤቶቼ ጋርና ረዳት የሌላቸውን ችግረኞችን ጭምር በመጋበዝ በዓሉን ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ"ብለዋል።

በዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ሻምበል ታሪኩ ንጉሴ እንዳሉት ግለኝነት እየተስፋፋና እያደገ መጥቷል፤  ይህ ደግሞ ችግር ሲገጥም ለብቻ ለመወጣት የሚያስችል ባለመሆኑ መቀራረብና በጋራ እንደ ቀድሞው አብሮነትን ማምጣት ይገባል።

የትንሳኤው በዓል ምክንያት በማድረግም በቤተ እምነታቸው  በኩል  አቅመ ደካማና ችግረኞች ለበዓል መዋያ  ድጋፍ የሚሆናቸው ገንዘብ  እያዋጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም