ህብረተሰቡ ለትንሳኤ በዓል እርድ ቆዳና ሌጦ እንዳይበላሽ በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርብ ተጠየቀ

83

መቀሌ  ሚያዝያ 17/2011  ህብረተሰቡ ለትንሳኤ በዓል በሚያከናውነው ዕርድ ቆዳና ሌጦ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ በማድረግ በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርብ በትግራይ ክልል የግብርና ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ጠየቁ።

ህብረተሰቡ ለትንሳኤ በዓል በሚያከናውነው ዕርድ ቆዳና ሌጦ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ በማድረግ በወቅቱ ለገበያ እንዲያቀርብ በትግራይ ክልል የግብርና ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ጠየቁ።ዕርድ በተፈፀመ በአራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ቆዳና ሌጦ ለገበያ መቅረብ እንዳለበት ተመልከቷል።
በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች አስተባባሪ አቶ ወልዱ ተስፋዬ እንደገለፁት ህብረተሰቡ ዕርድ ሲያከናውን ቆዳና ሌጦ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ ሊያስገባ ይገባል።


"በእርድ ወቅት ከስጋ ባለፈ ለቆዳና ሌጦ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል" ያሉት አስተባባሪው ቢሮው ከዕርድ ወቅት እስከ ገበያ ማቅረብ ባለው ሂደት ለቆዳና ሌጦ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ለህብረተሰቡ  ግንዛቤ ሲሰጥ መቆየቱን አሰታውሰዋል።


ህብረተሰቡ በበዓሉ በሚከናወኑ ዕርዶች ቆዳና ሌጦ ሳይበላሽ ፈጥኖ ወደ ገበያ በማቅረብ በገበያ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስተባባሪው ጠይቀዋል።

በዘርፉ ንግድ ስራ የተሰማሩ አቶ ሄኖክ ገብሩ በበኩላቸው "ዕርድ በተከናወነ በአራት ሰዓት ውሰጥ ቆዳና ሌጦ ለገበያ ሊቀርብ ይገባል " ብለዋል ።

በአለም አቀፍ የወቅቱ ገበያ ምክንያት የቆዳና ሌጦ ዋጋ የወረደ ቢሆንም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ወቅታዊ ገቢ ማጣት ስለማይገባ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደረግ የጠየቁት ደግሞ በዘርፉ ንግድ ስራ የተሰማሩ አቶ አታክልቲ አፅብሃ ናቸው።

"ጥራት ያለው የቆዳና ሌጦ ምርት ለማግኘት እንስሳትን አስሮ ከመቀለብና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ይጀምራል" ያሉት አቶ አታክልቲ በዕርድ ወቅትም ጥንቃቄ ካልተደረገ የሀገር ሃብትለብክነት እንደሚዳረግ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 ከክልሉ በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን 600ሺህ  ቆዳና ሌጦ ለገበያ እንደሚቀርብ   የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው  የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ዶክተር ገብሩ ለገሰ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአንድ ሚሊዮን በላይ  ቆዳና ሌጦ ቀርቧል።

በክልሉ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ የዕርድ እንስሳት ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የተናገሩት ዳይሬክተሩ ባለፉት ዓመታት የነበረው የእንስሳት ቆዳ በሽታ ጥቃት ሳቢያ አሁን ላይ መቀነሱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም