የኮንትሮባንድ አንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ክልሎችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው-የጉምሩክ ኮሚሽን

50


ሚያዝያ 17/2011 የኮንትሮባንድ አንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ክልሎችን ያሳተፈ ስራ እያከናወነ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተወያይተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ኮሚሽኑ አንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከጥቅምት ወር 2011 ጀምሮ የህግ ማዕቀፎችንና አደረጃጀቶችን ዘርግቷል።

ኮሚሽኑ ባደራጃቸው 14 ቅርንጫፎችና 96 መቆጣጠሪያ ኬላዎች አማካይነት ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን የመጠበቅና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የአፋር ክልል ዋነኛው የአገሪቱ የገቢና ወጪ የንግድ መስመር መሆኑን ያወሱት ኮሚሽነሩ፣ ክልሉ የአሰብ ወደብ ወደ ስራ ሲገባም በአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚኖረውን ድርሻ ያሳድገዋል ብለዋል።

ክልሉ ለኮንትሮባንድ ንግድ ያለዉን ተጋላጭነት ከግምት በማስገባት በቡሬና ታጁራ የተገነቡት ተጨማሪ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የተመረቁ 100 የክልሉ ተወላጆችን እንደሚቀጥርም አቶ ደበሌ አስታውቀዋል።

ክልሉ 40 የጉምሩክ አስተላላፊነት ፈቃድ የሚወስዱ ባለሙያዎች መልምሎ ሲያቀርብ ኮሚሽኑ አሰልጥኖ ወደ  ስራ እንደሚያሰማራቸው አብራርተዋል።

የአፋር ባለሀብቶች በገቢና ወጪ ንግዱ ዘርፍ እንዲሳተፉ ክልሉ በስልጠናና ተጓዳኝ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት እንዲያግዝ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሁሉንም ዜጎች ያማከለ አሳታፊ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የወሰደዉ አርምጃ ሌሎች ተቋማት በአስተማሪነቱ ሊወስዱት  ይገባል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ በተቋሙ ላይ የባለቤትነት ስሜትን በመፍጠርና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ለመከላከል ድርሻቸዉን አንዲወጡ መነቃቃት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በክልሉ አሁን በሥራ ላይ ያሉት የአዋሽ፤የጋላፊና ሚሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም