ለፋሲካ በዓል መሰረታዊ ሸቀጦች በበቂ መጠን እየገቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ

63

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 መጪውን የፋሲካ በዓል አስመልክቶ መሰረታዊ ሸቀጦች በበቂ መጠን እየገቡ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ህብረተሰቡ ለበዓሉ የሚፈልጋቸው ሸቀጦች እጥረት እንዳይገጥመው ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ እንደገለጹት፤ ለፋሲካ በዓል የሚሆን በቂ የሸቀጣሸቀጥ አቅርቦት ይኖራል።

ከበዓል ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የአቅርቦት ፍላጎት በመኖሩ የስኳር፣ የምግብ ዘይትና ዱቄት በበቂ መጠን ለህብረተሰቡ ማድረስ በሚቻልበት መልኩ አቅርቦት እንደሚኖር ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ በበኩላቸው በዓሉን አስመልክቶ በድጎማ ከሚቀርቡ ሸቀጦች በተጨማሪ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዶሮ እና የስጋ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

ሸቀጦቹ ወደ ህብረተሰቡ የሚያደርሱ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት 10 ዩኒዬኖችና 143 መሰረታዊ ማህበራት መኖራቸውን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

በዚህም ለበአሉ 25 ሺህ ዶሮዎች ለማስገባት የታቀደ ሲሆን እስካሁን 3 ሺህ 650 ዶሮዎች፣ ከ562 ሺህ በላይ እንቁላል፣ 7ሺህ ኩንታል ሽንኩርት ወደ ከተማዋ ገብቷል።

ዘንድሮ የሽንኩርት ዋጋ ጭማሪ የታየበት መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛቸው ዝናብ በመኖሩ የተነሳ የትራንስፖርት አስቸጋሪ መሆን በዋጋ ላይ ጭማሪ ማስከተሉን ጠቁመዋል።

ከድጎማ ውጪ  ወደ 690ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ከተማዋ የገባ ሲሆን በተለይ የዘይት እጥረት አለባቸው የተባሉ የንፋስ ስልክ፣ ልደታና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ላይ ይሰራጫል።

የስጋ አቅርቦትን በተመለከተ 225 ልኳንዳ ቤቶች ተዘጋጅተው እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

የንግድ ቢሮ ግብረ ኃይል አደራጅቶ ከበዓል ግብይት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም