ምዕመኑ የጸሎተ ሐሙስን ማህበራዊና ታሪካዊ አስተምህሮቶች ተግባራዊ እንዲያደርግ ተጠየቀ

133

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 ምዕመኑ የጸሎተ ሐሙስን ማህበራዊና ታሪካዊ አስተምዕሮቶች ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

ፀሎተ ሐሙስ (ህፅበተ እግር) በዓል ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተከብሯል።


ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች ጸሎተ-ሐሙስ ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ ማህበራዊና ታሪካዊ አስተምዕሮቶች እንዳሉት ገልጸዋል።


እነዚህን የፍቅር፣ የመተባበር፣ የሰላምና የትህትና ማህበራዊና ታሪካዊ አስተምዕሮቶችን ምዕመኑ ወደ ህይወቱ በመቀየር ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።


በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን የፀሎተ ሃሙስን በዓል ሲያከብሩ ያገኘናቸው ምዕመናን ኢትዮጵያውያን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ማህበራዊ ትስስራቸውን ጠብቀው ሊያቆዩት እንደሚገባ ገልጸዋል።


በተለይ ጸሎተ ሃሙስን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ የሃይማኖቱን አስተምዕሮ ወደ ራሳችን ህይወት በመቀየር በተግባር ማሳየት አለብን ብለዋል።

በአዲስ አበባ አገረ ስብከት የፓትሪያሪኩ ረዳት ሊቀጳጳስና የጉራጌ ጳጳስ ብጹህ አቡነ መልከ ጸዲቅ እንዲሁም የደቡብ ኦሞ አገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ፊሊጶስ ዛሬ የተከበረው ጸሎተ ሐሙስ ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ ማህበራዊና ታሪካዊ አስተምህሮቶች እንዳሉት ገልጸዋል።

አስተምህሮቶቹን ጠብቆ ማቆየት ለሰው ልጆች ስጋዊና መንፈሳዊ ደስታን ከመስጠት ባለፈ ኢትዮጵያውያን በአለም ላይ የሚታወቁበትን መልካም ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሆነም ተናግረዋል።

የ2011 ዓም የፀሎተ ሐሙስ (ህፅበተ እግር) በዓል ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሯል።