ኢትዮጵያውያን የትንሳዔን በዓልን በፍቅር በማክበር አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

67


አሶሳ ሚያዚያ 15 / 2011 ኢትዮጵያውያን የትንሳዔን በዓልን በፍቅር በማክበር አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ፡፡ 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአሶሳ፣ ጋምቤላ ምዕራብ ወለጋና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ በዓሉን አስመልከቶ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በዓሉን  ባህልና ወጉን በጠበቀ መልኩ በማክበር ኢትዮጵያዊነትን ሊያጠናክሩ ይገባል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር በሙሉ ራሱን በፍቅር አሳልፎ  እንደሰጠ አስታውሰው፣የበዓሉን መንፈስ በመጋራት በአንድነትና በፍቅር መቆም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በግጭት ምክንያት ወደ ተፈናቀሉ ዜጎች በመውረድ እርቀ ሠላም ማውረድና ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራን በማከናወን የለውጡን እንቅፋቶች ማስወገድ አለብን ብለዋል፡፡ 

ህዝበ ክርስቲያኑም በዓሉን ሲያከብር የዚሁ በጎ ምግባር ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል አስገንዝበዋል፡፡

ብጹዕነታቸው እንደሚሉት በተለይም ወጣቱ ያለአግባብ በመበልጸግ ጮማን ከመቁረጥ ይልቅ ቆሎ ቆርጥሞ የአገሩን ህልውና ማስቀጠል  አለበት፡፡

“ታሪካዊቷ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዛሬም የኢትዮጵያን አንድነት እየሰበከች ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፣ “ጥቂት ግለሰቦች ግን ቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ እስከ ማቃጠል የደረሰ ግፍ ሲፈጽሙ ይታያል” ብለዋል፡፡

ሕሊናቸውን በገንዘብ በመሸጥ እርስ በርስ የሚያጋጩትን ሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሚቃወማቸውም አቡነ ሩፋኤል ጠይቀዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎች መቀመጫቸውን ከተማ ከማድረግ ይልቅ ጾምና ጸሎት በማድረግና ምዕመናንን በመምከርና በማስተማር እንዲበረቱ መክረዋል፡፡

የትንሳዔ በዓል የፊታችን እሁድ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም