በለጋምቦ ወረዳ 900 የሽጉጥ ጥይቶች ተያዙ

52


ደሴ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 900 የሽጉጥ ጥይቶች መያዙን ፖሊስ አሰታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር መሐመድ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥይቶቹ የተያዙት ትናንት ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ ወረዳውን አቋርጦ ወደ ሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ ሲያመራ ነው።

"በለጋምቦ ወረዳ 022 ቀበሌ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ተይዟል" ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል ።

ጥይቶች የተያዙት የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-23568 አዲስ አበባ በሆነ የጭነት ተሽከርካሪ  ሲጓጓዙ ነው ብለዋል።

አሽከርካሪውና ሌላ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ኮማንደር መሐመድ አስታውቀዋል።

ከተጠርጣሪዎች  አንዱ ሁለት  መታወቂያ ካርዶች ይዞ መገኘቱንም አስታውቀዋል ።

ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ወንጀልን በመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ ኃላፊው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም