ኤምባሲው ሰው ካልመጣበት ንብ የሌለው ቀፎ ነው - አምባሳደር መለስ ዓለም

165

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2011 በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰው ካልመጣበት ንብ የሌለው ቀፎ ማለት ነው ሲሉ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።

በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኤምባሲውን እንደቤታቸው እንዲመለከቱት ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ይናገራሉ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ።

አምባሳደር መለስ ዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኤምባሲው በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች መብታቸውና ክብራቸው እንዲጠበቅ የማድረግ ሃላፊነቱን ለመወጣት የተለያየ የድጋፍ ስራዎችን ይሰራል።

ኢትዮጵያዊ ሲታሰር አገር የታሰረ ያህል በመቆርቆር ከኬንያ መንግስት ጋር በመስራት ለዜጎች መብት መከበር እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ኤምባሲው በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስን እንግልትና ሌሎች ጉዳቶችን ለመከላከልም ከኬንያ ኢምግሬሽንና የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ኬንያ የሚገኙና በስደት ላይ ያሉ፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስራ ላይ የተሰማሩ፣ በንግድ ላይ የተሰማሩና  መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ያሉትን ኢትዮጵያውያን ከኤምባሲው ጋር የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራም ነው አምባሳደሩ የሚናገሩት።

ዜጎች መንግስት በማንኛውም ጊዜ እንደሚደርስላቸው እንዲያምኑ ለማድረግ የተለያየ ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት አምባሳደር መለስ ''ኤምባሲው ዜጎች ሲደሰቱና ሲከፉ የሚመጡበት የራሳቸው ቤት መሆን ይገባዋልም'' ብለዋል።

''ኤምባሲው ሰው ካልመጣበት ንብ የሌለው ቀፎ ነው።'' ያሉት አምባሳደር መለስ፤ ዜጎች ልደት፣ ሰርግና ሌሎች ድግሶች ሲኖራቸውም እንኳን በኤምባሲው እንዲጠቀሙ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹላቸው ተናግረዋል።

በመጪው ቅዳሜ አንድ በኬንያ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የሰርጉን የፎቶ ስነ ስርዓት በኤምባሲው እንዲያካሂድ ከመግባባት ለይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል አምባሳደሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥር 6 ቀን 2011ዓ.ም “ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ኤምባሲዎች ለዜጎች ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተቋቋመው በ1964 ዓ.ም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም