የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በአዋጁ መሰረት አለመስተናገድ ለኪሳራ እየዳረገን ነው-የተሽከርካሪ ባለንብረቶች

101

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 ደረቅ ወደቦች የተቀመጠላቸውን የ24 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠታቸው መንግስትና ባለንብረቶችን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው::

ደረቅ ወደቦች የተቀመጠላቸውን የ24 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠታቸው የደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ማግኘት ያለባቸውን ገቢ እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ተናገሩ።

በተለይም ባለፉት 9 ወራት ባሉ አርባ እሁዶች ባለመሰራቱ ብቻ ባለሃብቱ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ማጣቱ ነው የተገለፀው።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በበኩላቸው  አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የወጪና ገቢ ምርቶችን በተመጣጣኝ የትራንስፖርት ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጓጉዘው ወደ ወደብና ከወደብ የማንሳት አቅምን ለማሳደግና ለተጠቃሚዎች እንዲቀርቡ ለማስቻል የዲመሬጅ አዋጅ ቁጥር 811/2006 ጸድቆ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።

የጭነት ላኪዎች፣ ተረካቢዎች፣ የመጫኛና የማራገፊያ አገልግሎት በሚሰጡ መጋዘኖችና ቁጥጥር በሚያከናውኑ አካላት የአሰራር ቅልጥፍና መጓደል የጭነት ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የስራ ጊዜ ብክነት የሚታይበት መሆኑም ለአዋጁ ተግባራዊነት መነሻ ነው።

አዋጁ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ የጫነውን እቃ በመግቢያ ወይም በመውጫ በር አሊያም በመተላለፊያ መንገድ የሚያደርገውን ቁጥጥር በአንድ ሰዓት እንዲሁም በመዳረሻ የጉምሩክ ጣቢያዎች ውስጥ የሚያደርገውን ደግሞ ከአራት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

በንግድ ሚኒስቴር ወይንም የተቆጣጣሪነት ስልጣን ባለው የመንግስት አካል የሚካሄድ የቁጥጥር ስራ ደግሞ በሶስት ሰዓት መጠናቀቅ አለበት ነው የሚለው አዋጁ።

ሆኖም አዋጁ በሚገባ ሁኔታ ስራ ላይ መዋሉን የሚከታተለው የትራንስፖርት ባለስልጣን እንደገለፀው ባለፉት 9 ወራት ባሉ 40 እሁዶች ባለመሰራቱ ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች 24 ሰዓት ያለስራ እንዲቆሙ አድርጓል።

የ24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት በኩል በተለይም የማራገፍ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ የሚገልፁት በባለስልጣኑ የዴመሬጅ ህግና ሎጅስቲክስ ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ አበበ እሸቱ ናቸው።

ባለስልጣኑን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሮቹን መፍታት እየቻሉ ባለመፍታታቸውና የቤት ስራቸውን ባለመወጣታቸው ጭነቶቹ ወደብ ላይ ቆይተው በሀገሪቷ ላይ ሌሎች ወጪዎችን ማስከተላቸውን ነው የሚናገሩት ዳይሬክተሩ።

አዋጁ በተቀመጠለት ሰዓት አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ቢደነግግም የቁጥጥር ስራ የሚያከነው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለምርት ጥራት ፍተሻ ቀናትን እየፈጀ እንደሆነ ነው ኃላፊው የነገሩን።

በተለይም ብረት የጫኑ ተሽከርሪዎች ለቀናት ያለስራ እየቆሙ መሆኑን በመግለፅ።

 ጋላፊና ሚሌ በመሳሰሉ ኬላዎች ላይ የ24 ሰዓታት አገልግሎት መስጠት ቢጀመርም በተለይም በአዳማ፣ በሞጆ፣ በድሬደዋና በቃሊቲ የመዳረሻ ጣቢያዎች ላይም የ24 ሰዓት የአገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ ውጤታማ ስራ መስራት እንዳልተቻለም ነው ያስረዱት።

የመድን ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ ዳኛው በበኩላቸው ማህበሩ ከ10 ዓመታት በላይ በዘርፉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ይናገራሉ።

ማህበሩ ባሉት ከ500 በላይ ተሽከርካሪዎች የተለያዩ እቃዎችን ከወደብና ወደ ወደብ የማጓጓዝ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ በርካታ ችግሮች እየገጠሟቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

የጅቡቲ መንገድ የተበላሸ መሆኑ፣ ዘመናዊ አሰራር አለመከተል፣ የደላላ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም በእቅድ ላይ የተመሰረተ ቅንጅታዊ የአሰራር ችግር መኖራቸውንም አንስተዋል አቶ ወርቅነህ።

ተቋማት በዲመሬጅ አዋጁ ባለው የጊዜ ስታንዳርድ መሰረት አገልግሎት አለመስጠታቸው ደግሞ በዘርፉ እየገጠማቸው ካሉት ችግሮች ዋነኛ መሆኑን በመግለፅ።

ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ብቻ በተለይ በመጫኛ ሳይሆን በማራገፊያ ቦታዎች ላይ እንደ ማዳበሪያ፣ ሬንጅና ብረት የጫኑ  ተሽከርካሪዎች ያለአግባብ በመቆማቸው ብቻ ማህበሩ ስምንት ሚሊዮን ብር ገደማ ሊያጣ እንደቻለም ነው ያስረዱት።

ባለሃብቱ በሰዓቱ ያለመስተናገዱ ደግሞ የዋጋ ንረትን በማስከተል ተጠቃሚው ኀብረተሰብ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይገበይ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ካልተቻለ ሀገሪቷ ቢዝነስን በቀላሉ ለመከወን የሚሰጣት ደረጃና የምትስበው ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ የሚያደርግ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገቢና ወጪ እቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ስምዖን የቁጥጥር ስራ የሚከወነው በእይታና በላቦራቶሪ ፍተሻ መሆኑን ገልፀዋል።

በእይታ በሚደረገው ፍተሻ ላይ የሚስተዋል ችግር አለመኖሩን አስረድተው የላቦራቶሪ ፍተሻ በሚደረግባቸው ምርቶች ላይ ግን የፍተሻ ውጤት ቀናት የሚፈጅ በመሆኑ በአዋጁ መሰረት ስራዎች እየተከናወኑ አለመሆናቸውን አልሸሸጉም።

ዲመሬጅን ለመቀነስ ከኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት ጋር በመሆን የላቦራቶሪን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ምርቶች ከሚመጡበት ሀገር ጥራታቸው ተረጋግጦ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ይዘው እንዲመጡ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የቃሊቲ ጉምሩክ የንግድ እቃዎች ኦፕሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረእግዚአብሄር ገብረፃዲቅ አገልግሎት እየተሰጠ ያለው ከሰኞ እስከ ዓርብ በመንግስት የስራ ሰዓት እንዲሁም ቅዳሜ ደግሞ እስከ 6፡30 ባለው ሰዓት እንደሆነ አስረድተዋል።

እስካሁን የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ያልተቻለው መሟላት ያለባቸው የቢሮ መሰረተ ልማቶችና የሰው ኃይል ማደራጀት በማስፈለጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ቅዳሜ ከሰዓትና እሁድ ያለመስራቱ አገልግሎት ፈላጊዎች በስታንዳርዱ መሰረት እንዳይስተናገዱ እንደሚያደርግ ገልፀው አስመጪዎች እቃው ከመድረሱ በፊት ሂደት በመጀመር የሰነድ ምርመራ የሚያደርጉበት ፕሪ አራይቫል አሰራር እንዳላቸውም አብራርተዋል።

በወራት ውስጥ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አንድ ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ደርሶ መልስ ስድስት ቀናት የሚፈጅበት ሲሆን አርባ እሁዶች ባለመሰራቱ ስድስት ጊዜ በላይ ደርሶ መልስ እንዳያደርግና ካለስራ እንዲቆም ያደርጋል።  

ዲመሬጅ ማለት የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ በላኪ፣ በተረካቢ ወይም በመጋዘን ለመጫኛና ለማራገፊያ እንዲሁም በመንግስት ተቆጣጣሪ አካል ለሚካሄድ የቁጥጥር ስራ ከተወሰነው የጊዜ ገደብ በላይ እንዲቆይ በመደረጉ ለባከነው ጊዜ መካካሻ የሚፈፀም ክፍያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም