የኢትዮ-ሱዳን የቢዝነስ ፎረም በቀጣይ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

126

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያና ሱዳን የቢዝነስ ፎረም በቀጣይ ሳምንት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃለ አቃባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በፎረሙ ከ150 በላይ የሱዳን ባለሃብቶች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የፎረሙ ዓላማም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር መሆኑን ጠቁመዋል።

ፎረሙን በካርቱም የኢትዮጰያ ኢምባሲ፣በኢትዮጵያ የሱዳን ኢምባሲና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ እንዳዘጋጁትም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በቀጣይ ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነጻነት ጉባኤ ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ ከተለያዩ አገራት መንግስታትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተውጣጡ ታዳሚዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታስተናግድ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው አገሪቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ላይ ያካሄደቸው ሪፎርም መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ዘንድሮ ለ26ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነፃነት ቀን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድረጅት /UNESCO/ እና ከአፍሪካህብረት ኮሚሽን ጋር በመሆን እንደሚያስተባበሩት ገልጸዋል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሚሲዮኖች ጉባኤውን አስመልክተው የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገ ዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የሚዲያ ነጻነት መለኪያ የደረጃ ሰንጠረዥን በቅርቡ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ከነበረችበት 40 ደረጃዎችን አሻሽላለች።

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ በሆነው ደረጃ መሰረት ከ180 አገሮች መካከል 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ነበር።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው መንግስት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ያለ ህጋዊ ሰነድ የሚኖሩትም በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቀጣይ የሚካሄዱ የቢዝነስ ፎረሞች እና የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም