የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ሊያሰባስቡ ነው

74

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በአገሪቷ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚሆን እስከ 100 ሚሊዮን ብር ሊያሰባስቡ ነው።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ዘርፉ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በተዘጋጀው እቅድ ላይ መክሯል።

በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮዊ ምክንያቶች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው። 

ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ሲሆን በቅርቡ ይፋ የሆነው መረጃ መሰረት በመላ አገሪቷ 3 ሚሊዮን የሚገመቱ ተፈናቅለው ለችግር ተዳርገዋል።

በመሆኑም እነዚህን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል እቅድ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል።

የትያትር ጥበባት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው በውይይቱ ወቅት እንዳሉት 250 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ናቸው።

በሁለቱ ከተማ መስተዳደሮችና ጠዘኙ ክልሎች በመዘዋወር የፊልም፣ ትያትር፣ ስዕልና ቅርጻ ቅርጽ፣ ግጥምና የፋሽን ሾው ስራዎችን በማቅረብ ገቢ ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።   

የመጸህፍት አውደ ርዕይ፣ ውይይቶችና ገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን የመርሃ ግብሩ አካል ሲሆኑ ከዝግጅቱ የሚገኘውን ገቢም ሙሉ በሙሉ ለተረጂዎች እንዲደርስ ይደረጋል።   

እንደ አቶ ጋሻው ገለፃ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ለዚህም ስኬት የየክልሎች ኃላፊዎች፣ ህብረተሰቡና ባለኃብቶች የዓላማውን በጎነት ተገንዝበው ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ አብሮነት፣ ፍቅርና መተሳሰብን የሚመለከቱ መልእክቶችን ለማስተላለፍም ታስቧል። 

የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩን ከሚያስፈፅሙት ኮሚቴዎች መካከል በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰብሳቢነት የሚመራውና ከዘጠኝ የኪነ ጥበብ ዘርፎች የተውጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ አንዱ ነው።

ለገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ  ከሚያዚያ 3 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም ቅደመ ዝግጅት የሚደረግ ሲሆን ከግንቦት 15 እስከ መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ለሦስት ወራት ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ እንዳለው ''የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም የሁሉም የዜግነት ግዴታ ነው''።

''ሁላችንም የምንደምቀው ንግስናችንም የሚያምረው ሕዝብ ሲኖር ነው፤ ያለሕዝብ ምንም ነን፤ሕዝብን ማገልገል ግዴታችን ነው፤ ስለ ሕዝብ መዝፈን ግጥም መግጠም ብቻ አይደለም ወርደን ከህዝቡ ጋር መታመም፣ ችግሩን መካፈል ይኖርብናል'' የሚል መልእክትም አስተላልፏል።

አርቲስት መሀመድ ሚፍታህ "አንዴ አናውራ" በሚል ርእስ ያዘጋጀው አዲስ ፊልም ገቢው ለተፈናቃዮች እንዲሆን ቃል ገብቷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ  ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሠላምና ማረጋጋት ለማጣት የኪነ ጥበብ ሙያ ወሳኝ ሚና አለው።  

ዘርፉን በመጠቀም የሚደረገውን ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ሚኒስቴሩ እንደሚደገፍ ጠቅሰው በጋራ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም