ከ80 በላይ የመድኃኒት ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

71

ሚያዝያ 17/2011 በመላ ሀገሪቱ የህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወነው ተግባር ከ80 በላይ የመድኃኒት ድርጅቶች ላይ እርምጀ መወሰዱን የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት የህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ዝውውርን ለማስቆምና ጥራት፣ ደህንነታቸው፣ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶችና የሕክምና መሳሪያዎች ላይ በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል  ህገ ወጥ ተግባር ሲፈፅሙ የተገኙ የመድኃኒት ድርጅቶች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እገዳና ፍቃዳቸው መሰረዙ ነው የተገለጸው፡፡

የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው፣ ምንጫቸው የማይታወቅ ፣ ለሌሎች ሀገሮች ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፣ የቅዝቃዜ ሰንሰለታቸውን ያልጠበቁ፣ በሀገሪቱ የመድኃኒት መዘርዘር ውስጥ ያልተካተቱና ያልተመዘገቡ፣ በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መድኃኒቶችና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ በተገኙ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

በቁጥጥር ወቅት ድርጅቶቹ ከደረጃ በላይ የሆኑ በርካታ መድኃኒቶችን እንዲሁም መንግሥት በእርዳታ ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን መድኃኒቶች ይዞ መገኘትን ያካትታል ብሏል ባለሥልጣኑ፡፡

ህገ ወጥ መድሃኒቶችን ሲያዘዋውሩና ሲነግዱ በነበሩ ተቋማት ላይ ተመጣጣኝና ሌሎችን በሚያስተምር መልኩ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ነው የገለጸው፡፡

መሥሪያ ቤቱ በመላው ሀገሪቱ እርምጃውን የወሰደው ከባለድርሻ አካላት፣ከኢንተርፖል፣ ከፌዴራልና ከክልል ፖሊስ፣ ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ነው፡፡

ቁጥጥሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ባለሥልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

ህብረተሰቡም የህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድና ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸም መጠቆም እንደሚገባም ባለሥልጣኑ አሳስቧል፡፡

የፍትህ አካላት፣ የክልል ተቆጣጣሪዎች የመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመስራት ለህብረተሰቡ ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች እንዲቀርቡ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም