በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ የተጠረጠሩ 22 ሰዎች በፍርድ ቤት ቀረቡ

78
ሐረር ሚያዝያ 17 /2011  በምስራቅ ሐረርጌ ዞን  በከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ዝርፊያ በመፈጸም የተጠረጠሩ 22 ሰዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በደንገጎ፣ሐረማያና ቀርሳ ወረዳዎች በሚገኙ ዳገታማ ቦታዎች ላይ ነው። የድሬዳዋ፣የሐረማያና የቀርሳ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በተያዙባቸው አካባቢዎች ባሉ ፍርድ ቤቶች እየታየ  መሆኑን አስረድተዋል። መምሪያው ትናንት በደንገጎ ቀበሌ  በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር  ለማዋል ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች በጉዞአቸው ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው በአካባቢ ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንዲጠቁሙ አሳስበዋል። በዞኑ አሽከርካሪዎችን በማስቆምም ሆነ በጉዞ ላይ የሚከናወኑ የወንጀል ደርጊቶችን ለማስቆም ከአጎራባች ክልሎች የጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ በአካባቢው ያልተከሰቱ ድርጊቶችን በማህበራዊ ሚዲያ እንደተደረገ አስመስሎ ከመለጠፍ እንዲቆጠብም ኮማንደር ስዩም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም