የተማሪዎች የስም ይቀየርልን ጥያቄ በፍርድ ቤቶች መደበኛ ስራ ላይ ጫና ፈጥሯል-

195
ሚያዝያ  17/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን ስማቸውን የሚቀይሩ ተማሪዎች መበራከት በፍርድ ቤቶች መደበኛ ስራ ላይ ጫና ማሳደሩን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለፁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍርድ ቤቶች ስማቸውን የሚቀይሩ ተማሪዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡ የተማሪዎች የስም ይቀየርልኝ ጥያቄ በተለይም የወረዳ ፍርድ ቤቶችን እያጨናነቁ መጥተዋል፡፡ "ማንኛውም ሰው በፈለገ ጊዜ ስም የመቀየር መብቱ እንዳለው በህግ የተደነገገ ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ የተማሪዎቹ የስም ቅየራ ከጎበዝ ተማሪዎች ፈተና ለመኮረጅ ዓላማ ያደረገ ስለመሆኑ የተደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል ። የተማሪዎቹ ጥያቄ በፍርድ ቤቶች የወንጀልና የፍትሃብሔር ጉዳዮችን ለማየት በፈጠረው የጊዜ ማጣበብ በመደበኛ ስራቸው ላይ ጫና እየፈጠረ በመሆኑን ተናግረዋል ። በዞኑ ትምህርት መምሪያ የፈተናዎች አስተዳደር ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አበበ እንዳሉት የተማሪዎች የስም ይቀየርልኝ ጥያቄ ባልተለመደ መንገድ እየጨመረ መጥቷል፡፡ "በመገባደድ ላይ ባለው የትምህርት ዘመን ብቻ ከ800 የሚበልጡ ተማሪዎች ስማቸውን ቀይረዋል"ያሉት ኃላፊው  የስም ቅየራው ካለፈው ዓመት በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል ። ስማቸውን የቀየሩ ከ95 በመቶ በላይ ተማሪዎች የ10ኛ እና የ12 ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን አመልክተዋል። የተማሪዎቹ የስም ቅየራ ዋና ዓላማ ፈተናን ከጎበዝ ተማሪ ለመኮረጅ ነው" ብለዋል ። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የተማሪዎች የስም ቅየራ እንዲቆም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያመለክትም ተግባራዊ ባለመሆኑ ድርጊቱን መከላከል እንዳልተቻለ ተናግረዋል። መንግስት የስም ቅየራንም ሆነ የተማሪዎች የአፈታተን ስልትን በአዲስ መንገድ መተግበር ካልቻለ ችግሩ ሊፈታ  እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ የደባይ ጥላት ግንድ  ወረዳ የቁይ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ይልቃል ደርበው በበኩላቸው      "ለሀገር አቀፍ ፈተናዎች መኮራረጅ ሲባል የስም ለውጦች ተበራክተዋል" ብለዋል። "ስም የሚቀይሩ በአብዛኛው ተማሪዎች  ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ናቸው" ያሉት መምህሩ ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ ካሉ ጎበዝ ተማሪዎች ጋር ስም ጋር በሚቀራረብ ስማቸውን እንደሚቀይሩ ጠቁመዋል ። የፈተና ጥያቄ ወረቀት ኮድ በመለያየትና ተቆጣጠሪዎችን በመመደብ ብቻ ኩረጃን ማስቀረት ስለማይቻል መንግስት ጠንከር ያለ አዲስ አሰራር ሊዘረጋ  እንደሚገባ አሳስበዋል። "ተማሪዎች ስም የሚቀይሩት ፈተና ለመቅዳት ነው" ያለው ደግሞ የሞጣ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ለወየው አካሉ ነው። የጎበዝ ተማሪ ስም አጥንተው በመቀየር ፈተና የሚኮርጁ ተማሪዎች  በራሳቸው አቅምና ጥረት የሚሰሩ ተማሪዎችን እየጎዱ መሆናቸውን ተናግሯል ፡፡ የሚመለከተው አካል ለችግሩ እልባት እንዲሰጥ ተማሪ ለወየው አመልክቷል። በዞኑ ከ47ሺህ በላይ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በተያዘው ዓመት  ብሄራዊ ፈተና እንደሚወስዱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም