ኢትዮጵያ ሃብት ለማፍራት ምቹ ከሆኑ ሃገራት ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች

89
ሚያዚያ 17/2011 ኢትዮጵያ ሃብት ለማፍራት ምቹ ከሆኑ ሃገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የግሎባል ዌልዝ ማይግሬሽን ሪቪው 2019 ሪፖርትን በመጥቀስ አፍሪካን ፕሬስ ኢጀንሲ ዘግቧል። መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ተቋም የአስር አመትን የሃብት ዕድገት ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ በመቶኛ ሲያሰላ ቻይናን በ130 በመቶ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲሰጣት ሞሪሽየስን በ124 ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮዽያ በ102 በመቶ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን  መረጃው  ጠቅሷል። ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚከወን ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ 204 ትሪሊዮን ዶላር አስተዋፅኦ አድርጋለች ማለት እንደሆነም መረጃው አመላክቷል። የኢትዮዽያ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሃብት በአስተማማኝ ሁኔታ ማደግ ለምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት እምቅ አቅም በመፍጠር ረገድም ሃገሪቷ ከደቡብ አፍሪካና ግብፅ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በቀጣዮቹ አስርተ አመታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የምታደርገው አስተዋፅኦ በ34 በመቶ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስነበበው ድረ ገፁ እኤአ በ2027 ዓ.ም መጨረሻም አስተዋፅኦው 3.1 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ጠቁሟል። የአለም የሃብት መጠን ባለፉት አስርተ አመታት ብቻ በ26 በመቶ ማደጉንና እኤአ በ2008 ከነበረበት 161 ትሪሊዮን ዶላር በ2018 መጨረሻ ላይ ወደ 204 ትሪሊዮን ዶላር መመንደጉን አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ በዘገባው አካቷል። እኤአ በ2028 የአለም የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሃብት በ43 በመቶ በማደግ 291 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችልም ሪፖርቱ አመላክቷል። አፍሪካም በግለሰብ ደረጃ እየተመራ ያለው ሃብት 2.3 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንም ሪፖርቱን ዋቢ በማድረግ ድረ ገፁ አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም