መንግስት ለደህንነት ስጋት የሚሆኑ ችግሮችን ከፈታላቸው ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ በጌዴኦ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ገለጹ

78
ሚያዝያ  17/2011 መንግስት ለደህንነት ስጋት የሚሆኑ ችግሮችን በመፍታት ሰላም እንዲሰፍን ካደረገ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን በጌዲኦ ዞን የተጠለሉ ተፈናቃዮች ተናገሩ፡፡ የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተፈናቃዮች ወደቄያቸው ተመልሰው የቀድሞ ሰላማዊ ኑሮቸውን መቀጠል በሚችሉበት ዙሪያ ትናንት የጋራ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በወይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የተፈናቃይ ተወካዮች እንዳሉት መንግስት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ካደረገ ወደነበሩበት ለመመለስ ይፈልጋሉ። ከተወካዮቹ መካከል አቶ ተፈራ በራቆ  በሰጡት አስተያየት "በተደጋጋሚ በደረሰብን መፈናቀል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተጋልጠናል "ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት  በምዕራብ ጉጂ ዞን በተቀሰቀሰው የጸጥታ ችግር ዜጎችን በማፈናቀል ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ  በህግ ቁጥጥር ስር ባልዋሉበት መመለሳቸው  ለደህንነታቸው  ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ጊዘያት መንግስት የህግ የበላይነትን ከማስከበር አንስቶ የመልሶ ማቋቋም ተግባርን ለማከናወን ቃል የገባ ቢሆንም በዚያ ልክ ባለመፈጻማቸው ለዳግም መፈናቀል እንዳጋለጣቸውም አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም መንግስት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፈተሸ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አለማየሁ በሪሶ በበኩላቸው የጉጂና የጌዲኦ ህዝብ ለዘመናት ተቻችሎ የኖረ የጋራ ባህልና ቀንቋ ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በደረሰባቸው የመፈናቀል አደጋ ሃብት ንብረታቸው በማጣታቸው ከመንግስት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳመለከቱት በችግሩ ልጆቸው  ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው ሊታገዙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡ "የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ባለፉት ጊዜያት ወደቄችን ስንመለስ ልማታችንን አልምተን እንዳንጠቀም ጥቃትና ጫና ደርሶብናል" ያሉት ደግሞ አቶ ጎበና ወሬራ ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱ ለዜጎች ያጎናጸፈውን ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት መንግስት እንዲያስከብርላቸውም ጠይቀዋል፡፡ "በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ጊዜያት የእርዳታ እህል መንግስት እየላከ የነበረ ቢሆንም ስርጭቱ ኢፍትሃዊ ከመሆኑም ባለፈ ቤተሰቦቻችን ለማቆየት የሚረዳ አልነበረም" ብለዋል፡፡ መንግሰት ተፈናቃዮችን እየደገፈ ማኖር ስለማይችል በዛላቂነት መቋቋም እንድንችል የጸጥታና የሰላም ጉዳይ ላይ በትኩረት መስራት እንደለበትም አመልክተዋ፡፡ መንግስት ለደህንነት ስጋት የሚሆኑ ችግሮች ከፈታላቸው ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ቱሳ በሰጡት ምላሽ "በሁለቱም ወገን ተፈናቃዮች አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት  ዜጎችን ወደቄቸው መመለስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡ ከጤና፣ ግብርና ከሰብአዊ ድጋፍ የተውጣጡ ከፍተኛ የአመራር ቡድን በምዕራብ ጉጂ ዞን በተለይም ቀርጫ ወረዳ ተፈናቃዮችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "በሃገር ደረጃ ዜጎችን ወደቀያቸው የመመለሱ ተግባር ወጥ በሆነ መንገድ እየተመራ ቢሆንም በጌዲኦ ተፈናቃዮች ተደጋጋሚ ጉዳት የደረሰ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮችን  ወደቀያችሁ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን መልሶም ለማቋቋም  የተጎዱ ቤቶችን ለመጠገን የሚያስችሉ ግብዓቶች በመቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ጉዳይ ዘላቂ ሰላሙን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ መንግስት በትኩረት እየሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በሁለቱም ወገን በጥፋተኝነት የተለዩ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ የፌደራል መንግስት ከሁለቱ ክልሎች ጋር በመቀናጀት የዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ህግ የማስከበር ስራው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቄያቸው መመለስ በማገዝና የጸጥታ አካላትን በመደገፉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ የመፈናቀሉ አደጋ እንደ ሃገር መንግስትንና ህዝብን የጎዳ መሆኑን ጠቁመው በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ችግሩ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተመሳሳይ መድረኮች በጌዲኦ ዞን አምስት መጠለያ ጣቢያዎችና በምዕራብ ጉጂ ዞን አንድ መጠለያ ጣቢያ ተካሂዷል፡፡ ከሚያዚያ 17 እስከ 30/2011ዓ.ም.  ባለው ጊዜው  በሁለቱም ወገን ያሉ ተፈናቃዮችን ሙሉ በሙሉ ወደቀያቸው ለመመለስ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም