በእግር ኳሱ ላይ የሚፈጠሩት ረብሻዎች በብሔርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ እየተመሰረቱ መጥተዋል-

70
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2011 በአገሪቱ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ላይ የሚፈጠሩት ረብሻዎች በብሔርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ እየተመሰረቱ መምጣታቸው  ተገለጸ፡፡ ክለቦች የፖለቲካ አመለካከቶቻቸውን የሚያንጸባርቁ ስሞች፣ አርማዎችና ምልክቶች ያሏቸው ከመሆናቸውም ባሻገር፤ እግር ኳስን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እያደረጉ መምጣታቸው ተጠቅሷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር "የስፖርት ጨዋነት ምንጮች" በሚል ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት ውይይት ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች መንስኤዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት  የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ጠቁሟል። በዚህም በውይይቱ የተሳተፉ አካላት ክለቦች የፖለቲካ አመለካከቶቻቸውን የሚያንጸባርቁ ስሞች፣ አርማዎችና ምልክቶች ያሏቸው ከመሆናቸውም ባሻገር፤ እግር ኳስን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እያደረጉ በመምጣታቸው በእግር ኳሱ ላይ የሚፈጠሩት ረብሻዎች በብሔርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው እየመጡ ይገኛሉ ብለዋል። በእነዚህ ምክንያቶችም ዘርን የተመለከቱ የኦሎምፒክ ቻርተርና የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ደንቦች እየተጣሱ መምጣታቸውም ይስተዋላል። በመሆኑም ስፖርት አንድነትን የሚያጠናክርና ህዝብንም የሚያፋቅር ትልቅ መሳሪያ በመሆኑ መንግሥት በዚህ ረገድ ያሉ ችግሮችን በመረዳትና ዓለም አቀፍ የስፖርት ሕግና ደንቦችን ለማክበር ይቻል ዘንድ ተገቢውን እርምጃዎች እንዲወስድ መድረኩ በሚከተሉት አቋሞች ላይ በጋራ ተስማምቷል:-  
  1. የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የዘር ልዩነት እንዲጠፋና የኦሊምፒክ ቻርተርና የኢንተርናሽናል ስፖርት ፌዴሬሽኖች ደንቦች እንዲከበሩ እንዲደረግ፤
 
  1. ዘርና ብሔርን መሠረት አድርገው የተቋቋሙት የእግር ኳስ ክለቦች ስማቸውን እንዲቀይሩ፤
 
  1. የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ስፖርት ፌዴሬሽኖች መሪዎችና አባሎች በዘራቸው ሳይሆን በሞያቸውና በችሎታቸው ብቻ እንዲመረጡ፤
 
  1. ስፖርት በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፋ የትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ፤
 
  1. የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ አገልጋዮች በጎ ፈቃደኞች በመሆናቸው ወጣቱ ትውልድ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሰለፍ እንዲበረታታ፤
 
  1. የኢትዮጵያን ስፖርት ድርጅቶች የሚያገለግሉ በስነ-ምግባር ኮሚቴዎች፣ በመንግሥት ፀጥታና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም በፖሊስና በፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩ፤
 
  1. ኢትዮጵያን በዓለም ስፖርት ጉባኤዎች የሚወክሉት አካላት ቢያንስ አንድ የውጭ አገር ቋንቋ አጣርተው የሚያውቁና ውይይቱን መከታተል የሚችሉ መሆናቸው እንዲረጋገጥ፤
 
  1. የፖሊስና የደህንነት ድርጅቶች የስፖርት ውድድሮችን በተለይ እግር ኳስ ጨዋታን በፀጥታና በጥበቃ መስክ ከፌዴሬሽኖቹ ጋር በመተባበር የሚሠሩ ቋሚ ኃላፊዎች በየከተሞቹ እንዲመደቡ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ፤
 
  1. በኢትዮጵያ ያሉት የስፖርት ስታዲዮሞችና መጫወቻ ስፍራዎች ተገቢ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የሕክምናና የአምቡላንስ አገልግሎትና እንዲሁም በቂ የመፀዳጃ ስፍራዎች እንዲኖራቸው፤
 
  1. የአልኮል መጠጥ በስታዲዮሞች ውስጥ እንዳይሸጥና ሲጃራ ማጨስ ክልክል መሆኑን እንዲታወጅ፤
 
  1. በኢትዮጵያ የሚዘጋጁት ውድድሮች ፎርማት ለክለቦች ተስማሚና ለስፖርት ዕድገት የሚጠቅም እንዲሆን እንዲደረግ፤
 
  1. መንግሥት እነዚህ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ የኦሊምፒክ ቻርተር አክባሪ እንዲሆን ተገቢውን ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ሲሉ የአቋም መግለጫቸውን አሳውቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሌሎች የስፖርት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረኩ የማጠቃለያው የአቋም መግለጫ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀርብም በጋራ ተስማምቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም