በዞኑ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች እየተገነቡ ነው።

54
ሚያዝያ 16/2011 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ  በ 18 ሚሊየን ብር ወጭ  ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኙ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን የዞኑ  መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ እዩአለም ምሳነው ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የህብረተቡን የመንገድ አቅርቦት ችግር በራስ አቅም ለመፍታት እየተሰራ ነው፡፡ በሰቆጣ ዙሪያ ስድስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሸሸረን-ባራ የመንገድ ስራ በአሁኑ ወቅት የአምስት ኪሎ ሜትር ግንባታ ሥራ ተጠናቋል። በጻግብጂ ወረዳ 18 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የጻታ-ሰላምጌ የመንገድ ሥራ ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ የአፈር ቆረጣ ሥራው መከናወኑን አስረድተዋል።፡ በደሃና ወረዳ የተክለሃይማኖት-ጉልድ-ጭርጉዝ የ14 ኪሎ ሜትር የቆረጣ ሥራ እና በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የመሃሪት-ባህር ጫኔ የ32 ኪሎ ሜትር መንገድ ቆረጣ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። ለመንገዶቹ ግንባታ ከሕብረተሰቡ የጉልበት አስተዋጽኦ በተጨማሪ መንግስት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን የጠቆሙት ቡድን መሪው በመንገድ ግንባታ ሥራው ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች በጉልበት እገዛ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።፡ ከአዳዲስ የመንገድ ሥራዎች በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ 56 የስትራክቸር ስራዎች እና 15 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠጠር የማልበስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የኒሯቅ - ተከዜ ሐይቅ የመንገድ ፕሮጀክት በክረምትም አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል 30 ሜትር እርዝመት ያለውን ድልድይ ግንባታ ሥራ በ18 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ መሆኑንና በመጪው ግንቦት ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የመንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አዘዘው በበኩላቸው መንገዶችን በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። የስሬል-ቄባ መንገድ የጎርፍ መውረጃ ቦይ ስራዎችን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግና የሸሸረን -ባራ መንገድ ስራ የቆረጣ ስራ እስከ ግንቦት ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። በወረዳው የቄባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ምልኬ አዳነ እንዳሉት ቀደም ሲል ቀበሌያቸውን ከዋና መንገድ የሚያገኝ መንገድ ባለመኖሩ ለእንግልት እና ለተለያዩ ችግሮ ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል። መንገዱ ከእዚህ ቀደም የድንገተኛ ህክምና ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ በአካባቢያቸው የአምቡላንስ አገልግሎትና የግብርና ግብዓቶችን በቅርበት እንዲያገኙ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ በወረዳው የባራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኪሮስ ደስታዬ በበኩላቸው የሚኖሩበትን አካባቢ ከዋና መንገድ ጋርም ሆነ ከሌሎች ቀበሌዎች ጋር የሚያስተሳስር የመንገድ ግንባታ ባለመኖሩ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ስታውሰዋል። የመንገድ ሥራው በተያዘለት ጊዜና በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንዲከናወን የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም