የኃይል መቆራረጥን በማስተካከል የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ---የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገለግሎት

52
ሚያዝያ15/2011 በትንሳኤ በዓል ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመቀነስና ሲከሰትም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት 24 ሰዓት እንዲሰሩ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገለግሎት ገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትንሳዔ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት በበዓሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል። በበዓላት ወቅት ከሚኖረው ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት አኳያ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ቢጠቀሙ የተሻለ ኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ይችላሉ፡፡ ይህም ገንዘብ ከመቆጠብ በተጨማሪ የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያለው፡፡ በትንሳኤ በዓል ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ለመቀነስና ሲከሰትም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት 24 ሰዓት እንዲሰሩ ዝግጅት ተደርጓል ብሏል፡፡ ሆኖም ከበዓሉ ጋር ተይያዞ በኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ ከፍተኛ የኃይል መጨናነቅ ሊከሰት ስለሚችል፤ ከዋናው ኃይል ቋት ከግሪድ/ ኃይል የሚያገኙ የድንጋይ ወፍጮ፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ሌዘር፣ የኬሚካል፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሌሎች የከፍተኛና የመካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች ከሚያዝያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ድረስ ኃይል ቀንሰው እንዲጠቀሙ ወይም ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ ትብብር ጠይቋል። ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ እና በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዳይከሰት ጥበቃ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡ ደንበኞች ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ሲፈልጉ አቅራቢያቸው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ እና በአማራጭነት በአዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞች በነፃ የጥሪ ማዕከል 905 በመደወል እንዲያሳውቁም ጠይቋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም