ወባን የማጥፋት ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሳይዘናጉ መስራት ይገባል .....ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

54
ሚያዝያ 16/2011   በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እየሆነ የመጣውን ወባን የማጥፋት ዘመቻ በስኬት ለመደምደም ሳይዘናጉ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ እየሆነ የመጣውን ወባን የማጥፋት ዘመቻ በስኬት ለማጠናቀቅ ሳይዘናጉ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወባን ለመከላከል የተሰሩ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው፡፡ በግምገማው ላይ የተሳተፉት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን እንደተናገሩት ወባን ለመከላከል በዘንድሮ ዓመት ብቻ ኬሚካል የተነከሩ 20 ሚሊዮን የአልጋ አጎበሮች በወባማ ሥፍራ ለሚኖሩ ሰዎች ተሰራጭተዋል፡፡ በተጨማሪም "ለወባ ትንኝ ተጋላጭ ለሆኑ 13 ሚሊዮን ነዋሪዎች የፀረ ወባ ኬሚካል የቤት ውስጥ ርጭት ተከናውኗል" ብለዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ህይወት ገለፃ ከመከላከሉና ከቁጥጥር ሥራ ጎን ለጎን የወባ ምርመራና ህክምና ተደራሽነት መስፋቱና ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በቅርበት እያገኘ መምጣቱ በበሽታው ሳቢያ የሚደርስን ሞት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ለአብነትም ከ2004 ዓ.ም እስከ 2009 ባሉት ዓመታት በወባ በሽታ የሚከሰት የሕሙማን ቁጥር 50 በመቶ፤ በበሽታው የሚደርስ ሞት ደግሞ 84 በመቶ በመቀነስ አበረታች ውጤት መገኘቱን ነው የገለፁት፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ወባ በወረርሽኝ መልክ አለመከሰቱ የቁጥጥር ሥራው ውጤታማነት ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል። እነዚህን ውጤቶች ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት የተጀመረው እንቅስቃሴ አካል እንድትሆን መደረጉን የገለጹት ወይዘሮ ህይወት፣ እ.ኤ.አ. በ2030 በሽታውን  ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ብሔራዊ ወባን የማጥፋት ፍኖተ ካርታ መነደፉን ገልጸዋል። "በእዚህም ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ ድሬዳዋን ጨምሮ በስድስት ክልሎች በሚገኙ 239 ወረዳዎች ሥራው ተጀምሯል " ብለዋል፡፡ በተገኘው ውጤት መዘናጋት ሳይፈጠር በተቀናጀ መንገድ በሽታውን የማጥፋቱ ጥረት በስኬት ማጠናቀቅ እንደሚገባ ወይዘሮ ሕይወት አስገንዝበዋል፡፡ የድሬዳዋ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፉአድ ከድር በበኩላቸው " በማዕከልና በክልል ደረጃ እንዲሁም በአጋር ድርጅቶችና በምርምር ተቋማት የተከናወኑ ሥራዎችን በጋራ መገምገሙ ወባን ለማጥፋት የተዘረጋውን ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ ያግዛል" ብለዋል፡፡ በድሬዳዋ ሕብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የመከላከል ሥራ መስራቱ፤ ኬሚካል የተነከረ አጎበር በየሦስት ዓመቱ መሰራጨቱና ተገቢው የሕክምና አገልግሎት ርቀው ለሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ጭምር ተደራሽ መደረጉ ከዓመታት በፊት በወባ ሳቢያ የሚደርስ ሞትና ህመም በአሁን ወቅት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሰ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ወባን ማጥፋት ከኔ ይጀምራል›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ግምገማ በሽታውን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማጥፋት በፊደራልና በክልሎች ደረጃ የተሰሩ ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጓል። ተወያዮቹም በተገኘው ውጤቶች መዘናጋት ሳይፈጠር በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ ብሔራዊ ወባን የማጥፋት ፍኖተ ካርታ በመመራት ስትራቱጂውን ዕውን ለማድረግ እንደሚረባረቡ አረጋግጠዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የማዕከል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪዎች እንዲሁም አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶችና የምርምር ተቋማት ተገኝተዋል፡፡   እስከ ነገ በሚቀጥለው ግምገማ ወባን ለማጥፋት የተኪያሄደ የምርምር ውጤት ለውይይት እንደሚቀርብም ታውቋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም